በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

160

ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተለያዩ ዘርፎች በሚካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የክልሉ ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።

በክልሉ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚዛን አማን ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ዛሬ ተጀምሯል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ  የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ መርሃግብሩን ሲያስጀምሩ እንዳሉት በተያዘው ክረምት የክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች በመቀናጀት ለ10 አቅመ ደካሞች አዲስ ቤት በመስራት ያስረክባሉ።

ቢሮዎቹም የክልሉ ትምህርት፣ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር፣ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች እንዲሁም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ለክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በክልሉ በኩል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም ጠቁመዋል።

 በቀጣይ በግብርናው፣ በጤናውና በሌሎች ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ የክልሉ ወጣቶች በመርሃ ግብሩ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቱ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራትና በማደስ፣ በችግኝ ተከላና ሌሎች ሥራዎችን በመስራት አገልግሎቱ እንዲያጠናክርም አስገንዝበዋል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉም ቢሮዎች የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግር ለማቃለል እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በጀት በክልሉ ለሚገኙ 32 አቅመ ደካማና አረጋውያን አዲስ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ታቅዶ ወደስራ መገባቱንም አስረድተዋል።  

ከዚህም በተጨማሪ የክልሉን ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር  2 ሺህ 500 የአቅመ ደካማ ያረጁ ቤቶችን ለማደስ መታቀዱን ነው የገለጸጹት።

ኃላፊው እንዳሉት በክልሉ ቤት እድሳትን ጨምሮ በ12 የአገልግሎት ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለመስራት ታቅዶ ወደተግባራዊ ሥራ ተገብቷል።

በሚዛን አማን ከተማ ቤት ከሚሰራላቸው አቅመ ደካሞች መካከል የአማን ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቄ መለሰ ብቸኛና አቅመ ደካማ በመሆናቸው የሣር ክዳን ቤታቸውን በቆርቆሮ ለመቀየር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር የሣር ክዳኑ ወደቤታቸው ውሃ በማስገባት በብርድ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ዛሬ ቤታቸው እንደአዲስ ሊሰራ መሆኑን ሲሰሙ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ሥራው እንዲፋጠንና መሰል ድጋፍም ለሌሎች እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በክልሉ የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁለት ወራት ጊዜ በላይ እንደሚቆይ ታውቋል።

በመርሃ ግብሩ ችግኝ መትክል፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያን ቤት ማደስና ሌሎችም ተጨማሪ ተግባራት ይከወናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም