በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ለነዳጅ የሚወጣ ከፍተኛ ውጭ ምንዛሬን ለመቀነስ እየተሰራ ነው

117

ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ለነዳጅ የሚወጣ ከፍተኛ ውጭ ምንዛሬን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

ሚኒስትሯ "ግሪን ቴክ አፍሪካ" በተሰኘ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ዛሬ ስራ አስጀምረዋል።

ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ ውስጥ ዘላቂና ለአካባቢ ተስማሚ የትራንስፖርት ስርዓትን መዘርጋት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል።

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ 4 ሺህ 800 አውቶብሶችን እና 148 ሺህ አውቶ ሞቢሎችን ጥቅም ላይ በማዋል ዘርፉን ወደ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይና ከጂኦተርማል የሚገኘውን የኃይል ምንጭ  እያደገ ከሚገኘው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂ ጋር በማጣጣም ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሂደት ኢትዮጵያን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ ለስኬቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተደራሽነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ዘይት ከሚሰሩት ጋር ሲነፃጸሩ የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹም የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው፣ የጥገና ወጪያቸው ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም ለነዳጅ ፍጆታ የሚወጣን ገንዘብ ማስቀረታቸው ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

ለተሽከርካሪዎቹ የሚውል የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ፍትሐዊና አስተማማኝ ለማድረግም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የግሪን ቴክ አፍሪካ ኩባንያ ኃላፊዋ ሲትራ አሊ፤ ኩባንያው በውጭና በሀገር ውስጥ በተግባር የተረጋገጡ ተሞክሮዎችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ በሽያጭና በኪራይ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገን አንስተዋል።

በቀጣይም ኩባንያው የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ተሽከርካሪዎቹ በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት በመቀነስ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ ያስቀመጠችውን ራዕይ ለማሳካት የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

በተለያየ መጠን ስራ የጀመሩት ተሽከርካሪዎች በመዲናዋ ለአንድ ወር የሚቆይ ነጻ የትራስፖርት አገልግሎት እና የማስተዋወቅ ስራ እንደሚያካሂዱም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም