የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው-ፖሊስ

174

ሐምሌ 06 ቀን 2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በክረምት ወራት ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያዬ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ይስተዋላል ፖሊስ ወንጀል ፈጻሚዎችን በመቆጣጠር ለፍርድ ከማቅረብ ጎን ለጎን ወንጀሎችን ከመፈጸማቸው በፊት ለመከላከል እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይደመጣል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመዲናዋ የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ ገልጸው፤ ወንጀሎችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በዚህ ወቅት የሚፈፀሙ የወንጀል ዓይነቶችን በመለየት ርምጃ ለመውሰድና ወንጀሎችን ለመከላከል ልዩ እቅድ ወጥቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶች በሚያጋጥሙት ወቅት ሊያደርገው ስለሚገባ ጥቆማና ስለሚተገበሩ ርምጃዎች ግንዛቤ የመስጠት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ከፀጥታ አንፃር አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲኖሩ ህብረተሰቡ ለየአካባቢው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት መረጃ የሚሰጥበት ትስስር መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

በከተማዋ በትራፊክ መብራቶችና በመንገድ ዳር ጎዳና ተዳዳሪ መስለው የቅሚያ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ፖሊስ በከተማዋ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ተፈፅመው ሲገኙም ርምጃ ለመውሰድ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ ማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ኦፕሬሽን መግባቱን ጠቅሰዋል።

የወንጀል ሁኔታን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም መቀነስ እንደሚቻል ከዚህ ቀደም በተሰሩ ሰራዎች ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት ምክትል ኮማንደር ማርቆስ።

አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል ለማድረግ ያሰቡ አካላትን ሴራ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን ማምከኑ አንዱ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

በክረምት ወቅትም የፀጥታ ችግሮችንና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ህብረተሰቡ መረጃዎችን ለፖሊስ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተለይም የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍትህ አካላት በማቅረብ የበኩሉን አስተዋፅኦ መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም