ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር ዝግጅት እያደረገች ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

104

ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ወይም የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከመደበኛው የመንግሥት ለመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ጎን ለጎን የሚተገበር መሆኑ ይታወቃል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት፤ ይህ አካሄድ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ነው።

የኃይማኖት መሪዎች፣ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች፣ የንግድ ዘርፍ መሪዎች፣ የሚዲያና  የትምህርት ተቋማትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ውስጥ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካሄድ ከነባሩ የዲፕሎማሲ መንገድ በተሻለ መልኩ በሕዝቦች መካከል ተዓማኒነት እንዳለው ነው የጠቆሙት አምባሳደር ዲና።

የአገርን ጥቅምና ፍላጎት በቀላሉ ለማስጠበቅና ለማስተዋወቅ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጫና የሚፈጥሩ አካላት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ትልቅ የዲፕሎማሲ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ይህን አካሄድ ከወታደራዊው የደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደሞከረችው አስታውሰዋል።

በወቅቱ ኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች በሰሜን አሜሪካና በተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ማከናወናቸውን አንስተዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት በግብጽና በሱዳን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር ጉብኝት ማድረጋቸውንም እንዲሁ።

ሆኖም እነዚህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ማሳተፍ ያለባቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ ማሳተፍ አለመቻላቸውን በውስንነት አንስተዋል።

መንግሥት እስካሁን የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ጠንካራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት።

የሚተገበረው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች ባሉበት ሁሉ የሚከናወን እንደሆነም ገልጸዋል።

በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አገራት፣ በኤሽያ፣ በአፍሪካና ሌሎች ወዳጆች ባሉባቸው አካባቢዎች ሥራው እንደሚጠናከር ጠቁመዋል።  

ለሂደቱ ስኬታማነት እንደ ባህልና ስፖርት፣ ቱሪዝም፣ ሰላም ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማትን እንደ ባለድርሻ ለማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥም ቢሆን በስድስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት መቋቋማቸውንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም