መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ችግር በሰላም አማራጭ እንዲፈታ መወሰኑ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያለውን ጽኑ አቋም ያሳየ ነው

111

ሐምሌ 6/2014(ኢዜአ) መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ችግር በሰላም አማራጭ እንዲፈታ መወሰኑ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያለውን ጽኑ አቋም ያሳየ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አካባቢዎች ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ገደማ በዘለቀው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች ደርሰዋል።

በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ ለአካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉት ዜጎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው።

ጦርነቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ያስከተለ ሲሆን፣ መንግስት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ተኩስ ማቆምን ጨምሮ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል።

መንግስት ከዚህም ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚመራ የሰላም አማራጭ እንዲሞከር ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ ሰይሞ ወደ ስራ ገብቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት ፈተና ለማውጣት የሰላም አማራጮችን ማየት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

መንግስት የዜጎች ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሁሉንም የሰላም አማራጮች ለመጠቀም ቁርጥኛ መሆኑን በማንሳት፣ የሰላም ንግግሮች ሂደትም ህግንና ስርዓትን ተከትሎ እንደሚደረግ ነው የጠቀሱት።

ከዚሁ ጎን ለጎን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥረት የሚያደርጉ ጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍ መንግስትና ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።

መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት ለማዞር አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በመንግስትና በሌላኛው ወገን የሚደረጉ የሰላም ንግግሮች በስኬት ከተጠናቀቁ ዜጎች ከስጋት ነጻ የሆነ የዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴያቸውን እንዲመሩ ያስችላል ነው ያሉት።

የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረጉ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተግባራትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በመጥቀስ።

የሰላም አማራጩ ስኬታማነት በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች የመልሶ ማቋቋም ትግበራን ለማፋጠን በር ይከፍታል ብለዋል።

የሰላም አማራጭ ውሳኔው በአጠቃላይ ለህዝቡ ሰላም ሲባል የተወሰደ ርምጃ ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ፣  እያንዳንዱ የሰላም አማራጩ አካሄድ ህግንና ስርዓትን ተከትሎ እንደሚፈጸም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም