በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር ብቻ 250 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

140

ባህርዳር ፤ሐምሌ 6/2014(ኢዜአ) በአራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በአማራ ክልል በአንድ ጀንበር 250 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር እየተካሄደ ነው ።

መረሃ ግብሩ የተጀመረው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር  በተገኙበት በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ "ሳባታሚት"   አካባቢ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት  ፤ ችግኝ  መትከል   የተፈጥሮ  ስነ ምህዳርንና የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ ዋነኛ መሳሪያ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር  የከርሰ  ምድር ውሃ በመጨመርና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

ዛሬ በሁሉም የክልሉ  ዞኖችና  ወረዳዎች  እስከ 11 ሰዓት  ድረስ  በሚካሄደው  የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 250 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት መላው  የክልሉ  ህዝብ  በነቂስ  በመውጣት  በዚህ ታሪካዊ  ዕለት የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።  

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው ፤ ክልሉ የታላላቅ ወንዞች መነሻ በመሆኑ የወንዞቹን ፍሰት ለመጨመርና ከደለል ለመከላከል ችግኝ መትከል አማራጭ እንደሌለው ገልጸዋል።

እስከ ነሐሴ 6/2014 ዓ.ም በሚካሄደው የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 1 ነጥብ አምስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አሁን ላይ ያለውን 15 ነጥብ ሶስት በመቶ የክልሉ የደን ሽፋን ወደ 15 ነጥብ ስምንት በመቶ ለማሳደግ እንደሚያስችል ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም