ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ

127
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ። ምክር ቤቱ 5ኛው የፓርላማ ዘመን ሦስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሄዷል። ምርጫው የተካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ላለፉት 30 ወሮች በአፈ ጉባኤነት የመሩት አፈ ጉባዔ ያለው አባተ በራሳቸው ፈቃድ መልቀቂያ በማቅረባቸው ነው። እርሳቸው ለምክር ቤቱ  "በራሴ ፍላጎት በአፈ ጉባኤነት አልቀጥልም፤ ነገር ግን በአባልነቴ እቀጥላለሁኝ" በማለት ጥያቄ አቅርበዋል። ምክር ቤቱ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ከአፈ-ጉባኤነት እንዲያሰናብታቸው የጠየቁት አቶ ያለው፤ ጥያቄውን "ለድርጅቴ አቅርቤ ተወያይተን በመግባባት ውሳኔ ላይ ደርሰንበታል" ብለዋል። ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በአራት ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል። የምክር ቤቱ አባላትም አቶ ያለው አባተ በአፈ-ጉባኤነታቸው ወቅት በምክር ቤቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመፈፀም ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። በምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ በአቶ መሓመድ ራሺድ አስመራጭነት የአዲስ አፈ ጉባኤ ምርጫ ተካሄዷል። ለምርጫውም ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ቀረቡ። ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በትግራይ ክልል በተመደቡበት የስራ መስክ "በብቃት፣ በተነሳሽነታቸውና በታታሪነታቸው የተመሰገኑና ለህዝብ ካላቸው አገልጋይነትና ቅንነት አኳያ በአፈ ጉባኤነት ቢመረጡ ምክር ቤቱን የመምራት ዓቅም አላቸው" የሚል ምሰክርነት ቀረበ። ምክር ቤቱም የወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ሹመትን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል። ወይዘሮ ኬሪያ ወደ አዲሱ ሹመት ከመምጣታቸው በፊት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው የቆዩ ሲሆን በቅርቡም የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊነት ተሾመው እያገለገሉ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም