ወጣቶች አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንዲሳተፉ ተጠየቀ

97

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር የበለጸገች አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

የአራተኛ ዙር የብሄራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና በጅማ ዩኒቨርስቲ ተጀምሯል።

በተያዘው የክረምት ወቅትም ይህ ስልጠና በጅማ፣ አዋሳ እና ዋቻሞ ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጥ ሲሆን 8 ሺህ በጎ ፈቃኛ ወጣቶችም ተሳታፊ ናቸው ተብሏል።

በጅማ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወጣቱ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ባለፉት ዘመናት ከአብሮነት ይልቅ ልዩነት፣ ከመረዳዳት ይልቅ በጥርጣሬ መተያየት እንዲኖር ሰፊ የጥላቻ ትምህርቶች ሲሰበኩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይ ወጣቱ በአገር አንድነት ጉዳይ በጋራ እንዳይሰራ እንዲሁም ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን እንዲለማመድ ሲደረግ ነበርም ብለዋል።

ሆኖም የዛሬ ዘመን ትውልድ ይህንን ታሪክ በመቀየር የኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ በአራተኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ከስልጠናው በኋላ የቀደመውን ታሪክ ለማስተካከልና ፍቅርና አንድነት እንዲኖር ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻም አገር መገንባት ማለት የህዝብን አንድነት እና እኩልነት ማጠናከር ማለት ነው።

''አገር ለመገንባት ሰላምን፣ ፍቅርንና መቻቻልን በህዝቦች መካከል ማስረጽ ይገባል'' ያሉት ሚኒስትሩ የሰላም አርማ ይዞ በሰላም እጦት ለሚሰቃዩ ህዝቦች በተግባር መድረስ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በጥላቻና በልዩነት የሚገነባ አገር እንደሌለም ገልፀው ለፍቅርና አንድነት መስፈን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

የጅማ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ለሰላም መስፈን የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ7 ሺ 400 በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሰልጠን ለአገር ሰላም መስፈን የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ዩኒቨርስቲው የሚጠበቅበትን የማህበረሰብ አገልግሎት በተግባር እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህ ስልጠናም ዩኒቨርስቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 3ሺ በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዩች ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ስልጠና ተሳታፊዎችም ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ በህዝቦች መካከል መግባባት እና አንድነት እንዲኖር የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ያገኙትን ትልቅ አጋጣሚም በኢትዮጵያ ዕድገትና ሰላም እንዲኖር የሚጠቀሙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም