ሥምምነቱ ሁሉም የጎረቤት አገራት አሸናፊ በሆኑበት አኳኋን ተጠናቋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

56
አዲስ አበባ  መስከረም 3/2011 ትላንት ምሽት የተደረሰው የደቡብ ሱዳን የሠላም ሥምምነት ሁሉም የጎረቤት አገራት አሸናፊ በሆኑበት አኳኋን መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ትላንት በአዲስ አበባ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መግሥታት (ኢጋድ) መሪነት የመጨረሻውን የሠላም ሥምምነት ፈጽመዋል። በሥምምነቱ ሠነድ መሰረት የአገሪቱ የሽግግር መንግሥቱ ስምንት ወራት የሽግግር ጊዜ ጨምሮ ሦስት ዓመት ሙሉ የሥራ ዘመን ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል። ይህንንም ተከትሎ ሳልቫ ኪር የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ተፎካካሪያቸው ሬክ ማቻር ደግሞ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን  እንዲያገለግሉም ተወስኗል። ሌሎች ተጨማሪ አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ቦታዎችም በዚሁ በአዲሱ የሥምምነት ሠነድ መሰረት ተጠቅሷል። ይህም የሽግግር መንግሥት የሥራ ጊዜውን ከማጠናቀቁ ስድስት  ቀናት ውስጥ የመጀመሪያውን ፍትሃዊ ምርጫና የሕዝብ ቆጠራ ማድረግ አለባት ተብሏል። የሽግግር መንግሥቱ መቀመጫውን በጁባ አድርጎ፤ ሕገ-መንግሥቱ ሳይሸራረፍ ተፈጻሚ እንዲሆን ክትትል እንዲያደርግም ኃላፊነት ተጥሎበታል። ተቋማዊ በሆነ መልኩ የአገሪቱን ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንዲያደርግም እንዲሁ። ይህንንና ሌሎችንም ተግባራት በማድረግ ደቡብ ሱዳን ጠንካራ የምስራቅ አፍሪካ አገር ለማድረግም በማለም ነው ትላንት ስምምነት ላይ የተደረሰው። ይህም የሠላም ሥምምነት የሁሉም የጎሮቤት አገራት አሸናፊ በሆኑበት አኳኋን መጠናቀቁን ነው የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የገለጹት። የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ኢትዮጵያን እንደሚመለከታት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ሥምምነቱ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል። ከዚህ ቀደም የነበረው የሠላም ሥምምነት ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ መሆኑን ጠቅሰው የአሁኑ ግን መሪዎቹም ይህንን ከግምት አስገብተዋል ነው ያሉት። ከአምስት ዓመት በፊት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ከመቶ ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ተሰደዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም