በአዲስ አበባ ያለበቂ ምክንያት ብጥብጥ የሚፈጥሩ አካላት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ፖሊስ አስጠነቀቀ

97
አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ያለበቂ ምክንያት ብጥብጥ የሚፈጥሩ አካላት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስጠነቀቀ። ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚሹ ሕገ-ወጥ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ እንደሚገባም  አሳስቧል። በመጪው ቅዳሜ  አዲስ አበባ ይገባሉ ተብለው ለሚጠበቁት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት አቀባበል ዝግጅት የሚያደርጉ የግንባሩ ደጋፊዎች በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች የድርጅቱ ዓርማ እንዲሰቀል የፌደራል ፖሊስ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል። ያም ሆኖ እነዚሁ አካላት በመንገዶችና ሌሎች የሕዝብ በሆኑ የጋራ ንብረቶች ላይ ቀለም መቀባትንና የነበረውን ሰንደቅ አላማ በማውረድ በሌላ የመተካት ተግባራቸውን ሊያቆሙ እንደሚገባም አስገንዝቧል። ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል አስቀድመው በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች አርማቸውን ለመስቀል እንዲችሉ ከፖሊስ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተዋል። "ነገር ግን እነዚህ ወገኖች በምንም አይነት የሌላውን ዓርማም ሆነ ሰንደቅ ዓላማ መንካትም ሆነ ማውረድ አይችሉም፤ የራስን መብት ሲያስከብሩ የሌላውንም ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ ይገባል፤" ብለዋል። ከዚህ ውጭ በመንቀሳቀስ ሕግን በሚጥሱና በሕዝብ የጋራ ንብረት ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም አስረድተዋል። "ሰንደቅ አላማና የድርጅት ዓርማ የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም፤ ነገር ግን ይሕንን አልፈው ሕግ የማያከብሩና በሕዝቡ ላይ አደጋ እየፈጠሩ ያሉ አካላትን ስርዓት ለማስያዝ እርምጃ ይወሰዳል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ወቅት ፖሊሲ የኦነግ አመራሮች የአቀባበል ስነ-ስርዓት በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም በመጠቆም። ወጣቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚሹ ሕገ-ወጥ አካላት መጠቀሚያ መሆን የለበትም ያሉት ኮሚሽነር ዘይኑ በኢትዮጵያ ነፃነት፣ ዴሞክራሲና ሰላም በዋናነት ተጠቃሚ የሚያደርገው ወጣቱን መሆኑንም ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም