የኢድ አል አድሃ( አረፋ) በዓል አንድነታቸውን በማጠናከር በጋራ ለማክበር ተዘጋጅተናል - የአሶሳ ነዋሪዎች

57

አሶሳ፤ ሐምሌ 01 / 2014 (ኢዜአ) ) ፡- ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር በጋራ ለማክበር መዘጋጀታቸውን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ የሚኖሩ የእስልምና እና የክርስት እምነት ተከታዮች ተናገሩ፡፡

የሙስሊምና  የክርስቲያን በዓላት  በጋራ ተሳስበውና  ተደጋግፈው አብረው ሲያከብሯቸው እንደኖሩ ነው  ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የገለጹት፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል  አቶ ኢብራሂም አዙቤር፤ የኢድ አል አድሃ( አረፋ) በዓል አቅም በፈቀደ ከሁሉም ሃይማኖቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ አንድታችንን ለማፍረስ የሚደረጉ ጥረቶችን ሀገር ተረካቢ ወጣቱ አጥብቆ እንዲታገል እና ክፉውን በመልካም እንዲያሸንፍ በመምከር  የድርሻቸውን እንደሚወጡ  አስረድተዋል፡፡

ይህም በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የሚደገፍ እንደሆነ ያመላከቱት፡፡

ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖት እና በብሄር ለያይቶ ለማጋጨት   በሚደረገው  ጥረት ጉዳት ቢያደርስብንም መቼም ሊሳካ አይችልም ሲሉ አቶ ኢብራሂም  ገልጸዋል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮያውያን አንድነትን የመረጡ እና ለዘመናትም በዚሁ ውስጥ የኖሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አንዳቸው የሌላቸው ሃይማኖት በማክበራቸው ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱም ያሉት  ደግሞ ቄስ መላከምህረት ገብረመስቀል ባህሩ ናቸው፡፡

በግላቸው በተለያዩ መስጊዶች በሚካሄዱ በዓላትም ሆነ ማህበራዊ ጉዳዮች ጭምር በነጻነት እንደሚሳተፉ ጠቅሰዋል፡፡

የየትኛውም ሃይማኖት በዓል በተለያየ መልክ ይከበር እንጂ በአንድ ሃገር እንደሚኖር ዜጋ የጋራ ነው ብለዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፤  ለዚህ ማሳያው የሃይማት ተቋም ሆነ የእምነቱ ተከታዮች የሚያከብሩት በዓል ሠላምን የሚሰብክ በመሆኑ ነው፡፡

በተለይም ወጣቶች ከስሜታዊነት በመራቅ በየሃይማኖቱ የተቀመጡ የመከባር እና የማቻቻል እሴቶችን በሚገባ ተግባራዊ ቢያደርጉ የገጠሙንን ፈተናዎች ማለፍ ያስችለናል ሲሉ መክረዋል፡፡

ወጣት ጀማል ጅብሪል በበኩሉ፤  የብዙ ሃይማኖት እና ማህበረሰብ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ለመከፋፈል የማትመች መሆኗ በገጠመን የጸጥታ ችግር ውስጥ ሆነን በመከባበር በመደጋገፍ ማየት ችለናል ብሏል፡፡

ይህን ለማስቀጠል ግን አንድታችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማጠናከር የግድ እና መሠረታዊ ጉዳይ ነው ሲል ገልጿል፡፡

በተለይም ወጣትነታችንን እንዴት እየተጠቀምን እንደሆነ እኛ ወጣቶች ራሳችንን በመጠየቅ የድርሻችን ማበርከት አለብን ብሏል ወጣቱ ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም