የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀትን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ

282

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት የ786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀትን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄዷል።

የምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2015 ዓ.ም የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት አስመልክቶ ሪፖርት አቅርቧል።

ከምክር ቤቱ አባላት በጀቱን አስመልክቶ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የ2015 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት የ786 ነጥብ 6 ቢሊዮብ ብር ረቂቅ በጀትን በአራት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

ምክር ቤቱም የቀረበውን በጀት አዋጅ ቁጥር 1275/2014 በሚል ነው ያጸደቀው።

የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የተያዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 218 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለካፒታል በጀት ተመድቧል፡፡

345 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፤ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ደግሞ ለክልል መንግስታት ድጋፍ እንደሚከፋፈል ተገልጿል።

ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

ከተመደበው በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮኑን ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙንና ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ36 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም