በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 10 ሄክታር መሬት የሸፈነ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሄደ

167

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 10 ሄክታር በሸፈነ መሬት ላይ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መካሄዱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል ህዝቡ ሰላሙን እየጠበቀ ሰፊ የችግኝ ተከላ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡የፓርኩ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዛሬ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የፓርኩ ክልል በሆኑት አዲስጌና ሚሊገብሳ ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ የፓርኩን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ የሚያግዙ ሀገር በቀል የሆኑ የሀበሻ ግራር፣ኮሶና አምጃ የተባሉ የዛፍ ዝርያዎች እንዲተከሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በዕለቱ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 90 ሺህ ያህል ችግኝ በ10 ሄክታር መሬት ላይ መካሄዱን አመልክተው፤በቀጣይም በ12 ሄክታር የሚሸፍን ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ ከተተከሉ 50 ሺህ ችግኞች 81 በመቶው በተደረገ እንክብካቤ ማፅደቅ መቻሉንም አቶ አበባው ጠቁመዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የፓርኩን ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅ እንዲቻል 25 ሄክታር የሸፈነ የደን ልማት ስራ መከናወኑንም አብራርተዋል።''ህዝባችን የክልሉን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳታፊ በመሆን በክረምቱ ወራት ሰፊ የችግኝ ተከላ ስራ እያከናወነ ይገኛል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው ናቸው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አለም አቀፍ ቅርስ እንደመሆኑ የፓርኩን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ የሚያግዙ ሀገር በቀል ችግኞች በመትከልና በመከባከብ ጭምር ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለአለም ፈንታሁን በበኩላቸው፤ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ በማጽደቅ ለትወልድ ማሻገር ይገባል ብለዋል።

ህዝቡ በፓርኩ ክልል የተተከሉ ችግኞችን በማረም፣ በመኮትኮትና በመጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከ20 ሺ በላይ የሚሆኑ የፓርኩ አዋሳኝ ወረዳ ነዋሪዎች ፣የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራም ነው፡፡

የሰሜን ተራራሮች ብሄራዊ ፓርክ በውስጡ 35 ዓይነት ብርቅዬ የዱር እንስሳት፤ 128 የአእዋፋትና ከ1ሺ 200 በላይ የእጸዋት ዝርያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም