"የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ምንም አይነት ንግግር አይኖርም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

114

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)መንግስት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ሲሞከር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚደረግ ንግግር አይኖርም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሠላምና ፀጥታ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን አቅርበዋል።

በቅርቡ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰናቸው ይታወሳል።

የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየትና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ህወሃት በሀገር አንድነትና በህዝብ ደህንነት ላይ የከፈተው ጦርነት ሀገራዊ ሆኖ እያለ በሰላም አማራጭ ሂደቱ ገዥው ፓርቲ ብቻውን ለመሳተፍ መወሰኑ ላይ የተገቢነት ጥያቄ አንስተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሃት ላይ የሽብርተኝነት ፍረጃውን ሳያነሳ ከሽብር ቡድን ጋር በሰላም አማራጩ ለመወያየት መወሰኑ ወንጀል አይሆንም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

"ለሰላምም ይሁን ለጦርነት የምንወስነው በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅሟን በሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ ካልተቻለ የህይወት ዋጋ ከፍለን በመስዋዕትነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት በሰላማዊ አማራጭ ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት መወሰኑ ክፋት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላምን መጥላት እንደማይገባ ተናግረዋል።

መንግስት ስለሰላማዊ አማራጩ ሌሎችን የመብትም ሆነ ሂደቱን በብቸኝነት የመከታተል ሙሉ ስልጣን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

ከወራት በፊት ሁሉም የመንግስት ሰራተኞችና ሁሉም ህዝብ በየክልሉ በሰላም ዙሪያ ተወያይቶ ችግሩን ከተቻለ በሰላም ይፈታ የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

"እኛ ባለመግባባታችን ምክንያት ጠላቶቻቸን ብዙ ጥፋት እያደረሱ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ጡት የሚነክሱ ሃይሎች በዚህ መንገድ መቀጠል እንደሌለባቸው ተናግረዋል።

የጠላትን ሴራ ከምንጩ ለማድረቅና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ሂደትን መሞከርና መነጋገር መልካም መሆኑን ጠቅሰው የሰላም ሂደቱ ስኬት በሂደት የሚታይ ይሆናል ነው ያሉት።

ህወሃት አሸባሪ በመሆኑ ከቡድኑ ጋር የሰላም ንግግር አያስፈልግም በሚል ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም "ደርግ ሁልጊዜ ከሻዕቢያና ከህወሃት ጋር ይደራደር እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው" ብለዋል።

በውጊያ ውስጥ ያሉ ሃይሎች ሁልጊዜ ይነጋገራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰላም ንግግርና ድርድር የሚካሄደው በድርድር ውስጥ ትርፍ ካለ ለማግኘት ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን፣መፈናቀሎችን እና የሰዎችን ሞት ለማስቆም የሰላም አማራጩን መሞከር ተገቢ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በገንዘብና በሚዲያ ከኢትዮጵያ የጠነከሩ ጠላቶች እየተረባረቡብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላማዊ መንገድ ጠብ አጫሪነትና ሀገር አፍራሽነታቸውን የሚያቆሙ ሃይሎች ካሉ እድል መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም