የምርት ገበያ የክፍያ ርክክብ ስርዓትን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከአባይ ባንክ ጋር ተፈራረመ

72
አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የክፍያ ርክክብ ስርዓትን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከአባይ ባንክ ጋር ተፈራረመ። ስምምነቱ ገዥዎች የሚገዙበትን ገንዘብ አስቀድመው ወደባንክ እንዲያስገቡ፤ ተገበያዮችም ግብይቱን በፈፀሙ ማግስት ለአቅራቢዎች የሸጡትበት ገንዘብ በቀጥታ ከገዥው የባንክ ሂሳብ ወደ ሂሳባቸው እንዲዘዋወርላቸው የሚያስችል ነው። ይህም አስተማማኝ የግብይት የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ የክፍያና ርክክብ ሥርዓቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ያደረጋልም ተብሏል። የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ እንደገለጹት ስምምነቱ በተለይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በምርት ገበያው በኩል እንዲገዛ ህጋዊ ዋስትና የሚሰጥ ነው። "ስርዓቱ ሻጮች የሸጡበትን ገንዘብ በእርግጠኝነት በምርት ገበያው በኩል እንደሚያገኙ ተማምነው ግብይታቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል" ሲሉም አብራርተዋል። አባይ ባንክ በዚህ መልኩ የሥራ ግንኙነት ከምርት ገበያው ጋር የመሰረተ 15ኛ ባንክ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል። የአሁኑ ስምምነት በክፍያ ስርዓቱ የሚንቀሳቀሰውን የባንክ አካውንትቶች ብዛት ወደ 5 ሺህ 500 በላይ ያደርሰዋል ሲሉም ተናግረዋል። የአባይ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ የኋላ ለገሠ በበኩላቸው እንደተናገሩት ባንካቸው በዚህ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ መካተቱ ለኢትዮጵያ የግብይት ሥራዓት መሻሻል የበኩሉን አስተዋጾኦ እንዲያበረክት ያስችለዋል። የዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ባንኩ በወቅቱ ለደንበኞች ክፍያ እንዲፈጽምና ደንበኞችም ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉት ያግዛቸዋል  ብለዋል። በተለይም የወጪ ምርትን በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት የተቀላጠፈ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል። የዛሬ 10 ዓመት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች 50 በመቶ ድርሻ እንዳለው ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እስካሁን ተቋሙ ባሉት 22 ቅርንጫፎች የጥራት ደረጃ ወጥቶላቸው 206 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው አምስት ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርት ተገበያይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም