የቱሪዝም ዘርፍ ማርሽ ቀያሪ—ታላቁ የህዳሴ ግድብ

953

በማደግ ላይ እንደሚገኙ ሌሎች ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም የዕድገት  ተስፋቸው የተመሰረተው በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ላይ ብቻ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ በሚቻልበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆኖ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ወቅት ያውም ለወንዙ መገኘት ዋና ምንጭ የሆነውች ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት እና ባልፈረመችው ስምምነት ላይ ተቸክሎ ስለተናጠል መብት እና ተጠቃሚነት ብቻ ማውራት ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር አብሮ መራመድ አለመቻልን ያሳያል፡፡ 

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለችው ከውሃ የሚገኝን የታዳሽ ሀይል አቅሟን ማሳደግ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት የሚካሔደውን ትግል በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ለማንም የተሰወረ አይደለም።የግድቡ መገንባት በሀይል አቅርቦት ዘርፍ ኢትዮጵያን በቀጣናው ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከማድረጉ በተጨማሪ ከኮይሻ፣ ከወንጪ እና ከጎርጎራ ፕሮጀክቶች ጋር በመተባበር በቱሪዝም ዘርፉም በዓለም ካሉ ቀዳሚ መዳረሻዎች መካከል አንዷ ያደርጋታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ይህንን አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግም በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አይኖቻቸውን ወደ ህዳሴ ግድብ ማማተር ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡

ከውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በየጊዜው ከሚሰማ ንትርክ ጎን ለጎንም ይህ ግድብ የግንባታ ሂደቱን በማገባደድ ሀይል ወደ ማመንጨት ደረጃ ከተሸጋገረም ሰንብቷል፡፡ በቅርቡም ሶስተኛውን ውሃ ሙሌት በስኬት በማከናወን ተጨማሪ የሀይል ምንጭ የሚሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱንም የሚወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀድሞ ጀምራም ሆነ ወደፊት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር መስራት ሁሉንም አሸናፊ እንደሚያደርግ በማመን አቋም ይዛ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳደግ አኳያም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሀይል ማመንጫነት ባለፈም አንዱ የዓለም የቱሪዝም ማእከል ሆኖ ብቅ የሚልበት እምቅ አቅም እንዳለው ግልጽ ነው።

ኢትዮጵያ ይህን ግድብ በማጠናቀቅ ፍሬውን እንዳታይ ማድረግ የታሪካዊ ጠላቶች የዘወትር ጥረት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ተጠቅማ መልማት ከቻለች የእኛ ህልውና ያበቃለታል ብለው የሚያምኑ ግብጽን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ዕድገቷ እንዳትመልስ ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ ለዚህም በዋናነት በሀገር ውስጥ ከተፈለፈሉ ‹ነጻ አውጪ› ነን ባይ ድርጅቶች ጋር ያለማቋረጥ በመስራት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ለማሳያነትም ሕወሃት ደርግን ባሸነፈ ጊዜ መጀመሪያ ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ የተደረገው የዓባይ ተፋሰስን ተከትለው የተሰሩ የፓዌ የጣና በለስ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግብጽ ኢትያጵያን የማዳከሚያ በማድረግ ስትከተለው የነበረው አንዱ ስልት በየዘመኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ አንደኛውን ወገን በመደገፍ ሰላም እንዲደፈርስ ማድረግ ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብም ሆነ ሌሎች ልማት ተኮር ፕሮጀክቶችን እንዳትገነባ ለማድረግም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ያሏትን ዜጎችና ደጋፊዎች በመጠቀም የተሻለ ድጋፍ እንዳታገኝ ስትሰራ መቆየቷ ብቻ ሳይሆን አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመች መሆኑ የአደባባይ ሚኒስጥር ነው፡፡  

የነሱ ስጋት ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ የውሃ እጥረት ይገጥመናል በሚል ብቻ አለመሆኑንና ይልቁኑም የግድቡን ግንባታ መጠናቀቅ ተከትሎ በሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ምክንያት ግብጽን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ይፈልሳሉ፣ ቀጣናዊ ተጽዕኖውም ይለወጣል ከሚል መነሻ እንደሆነም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን እና ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በግድቡ ምክንያት ከሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሚገኘው የዓሳ ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንደሚሆንም አያጠራጥርም። ከዚህ በተጨማሪም የሚፈጠረውን የቱሪስት መስህብነት ታሳቢ በማድረግ ከወዲሁ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ እና በቱሪዙም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እና ልምዱ ያላቸውን ባለሀብቶች ትኩረት እና ቀልብ መሳቡ አይቀርም።

ከመነሻው ጀምሮ የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሃብቷ የመልማት መብትና ፍላጎት በጥርጣሬ የሚመለከቱ አካላት ግድቡ እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ የቻሉትን ሁሉ ሲያደርጉ መቆየታቸው የታወቀ ጉዳይ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጋግዞና ተባብሮ በጋራ መልማትን የምታስቀድመው ሃገራችን ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ይበልጥ በሚያጠናክር መሰል ፕሮጀክት ላይ ያላትን አቅም ሁሉ አሟጣ መስራቷ መሰረታዊ መነሻው ይሄ ቢሆንም እኔ ብቻ ልጥቀም ዘላለማዊ ድህነትን ተከናንባችሁ ዝለቁ የሚሉ አካላት በውስጥም በውጭም ጫና ለመፍጠር መሞከራቸውን ቀጥለዋል።የአሜሪካው የቀድሞ ዲፕሎማት ቲቦርናዢ በግል ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ለአባይ ተፋሰስ አንድ ጠብታ ውሃ የማታበረክተው ግብጽ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ መቶ በመቶ የመወሰን መብት ሊኖራት አይችልም፡፡ I follow the passionate discussion on the #GERD with interest.  But the fundamental truth is – a country which does not contribute one drop of water to the Nile (#Egypt) – cannot demand 100% of the right to decide how the waters should be used by all.  The world has changed  ማለታቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ እውነታ ባለበት ጭምር ነው ኢትዮጵያ ግድቡን ከመገንባት፣ ውሃም ከመያዝና ሀይል ከማመንጨት የሚያግደኝ አንዳች ምድራዊ ሀይል የለም፤ የሚያዋጣው በጋራ ሰርተን በጋራ መልማትና ማደግ ብቻ ነው በሚል እሳቤ እየተንቀሳቀሰች ያለችው፡፡ ለዚህም ግድቡ እየተገነባ ካለበት አካባቢ ሀይል ወደ አካባቢው ሀገራት በቀላሉ ማስተላለፍ የሚያስችሉ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች እየዘረጋች መሆኑን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባለፈ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት የሚያበረክተውን የአገልግሎት ዘመን ለማራዘምም ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል መከላከልን ጨምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በማዘጋጀት በሁሉም የሃገራችን ክፍል መላ ህዝቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ህዝባዊ ንቅናቄ ማካሄድ ከጀመረ እነሆ አራት አመት ሆኖታል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ተግባር ላይ የጎረቤት ሀገራትም ተሳተፎ እንዲኖራቸው ችግኞችን ለየሀገራቱ በድጋፍ መልክ እየቀረበ መሆኑ አንዱ የጋራ ልማትና ጥቅም ማረጋገጫ መንገድ ነው።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአረቡን መገናኛ ብዙሃን በቅርበት የሚከታተሉት የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል እና ዑስታዝ ጀማል በሽር ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ትልም ከዳር ማድረስ እንድትችል ታሪካዊ ጠላቶች የውስጥ እና የውጭ ተላላኪዎችን በመጠቀም የሚከተሉትን አፍራሽ ሴራዎች በጋራ በመቆም መመከት እንደሚገባ  መግለጻቸው ይታወሳል።

በሃገራችን ልማት ዙሪያ የሚከናወንን የተጠና አፍራሽ አካሄድ ህብረተሰቡ በውል በመረዳትና አንድነቱን በማጠናከር በጋራ መከላከል ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። የህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስራን በሚገባ በማሳካት ከሃይል አቅርቦቱና በቱሪዝም ዘርፉ ከሚገኘው መጻኢ ብሩህ ተስፋ ባሻገር የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚፈጠረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ እንደተረባረበበት ሁሉ ፍጻሜውን ለማሳካት ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል የወቅቱ ሃገራዊ ግዴታ ነው።