በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች ከ196 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል

141

ሰኔ 28/2014 (ኢዜአ) በአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች ከ196 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

“አሻራችን ለከተሞቻችን፣ ለትውልድ እንስራ፤ ለኢትዮጵያ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ከተሞች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ዛሬ በለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ ተካሂዷል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፤ በከተሞች ውስጥ የሚተከሉ ችግኞች በአብዛኛው ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን እንዲጸድቁም የመንከባከብ ኃላፊነት የሁሉም መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የተያዘው ግብ እንዲሳካ ከተሞች ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች 196 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ነው ወይዘሮ ጫልቱ የጠቆሙት።

የአየር ንብረት ለውጥ የአገራችንና የዓለም ከፍተኛ ፈተና መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ጫልቱ፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያካሄደች መሆኑንም ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ድንበር እንዲሻገር ለምሥራቅ አፍሪካና ለጎረቤቶቿ እየሰራች መሆኗን አስታውሰዋል።

የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ለማሳካት የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከተሞች የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ የመንከባከብ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

አቶ በሪሶ አያይዘውም ለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ብቻ ሳይሆን የሰላምና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተምሣሌት መሆኗንም ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ከተሞች ለአረንጓዴ አሻራ ያላቸው ሚና፣ የምግብ ዋስትናን ያረጋገጠ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ማስቀጠልና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ማረጋገጥ የሚያስችል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ዉይይት ተደረጎበታል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም