የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሙከራ ፕሮጀክትን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

67

ሰኔ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሙከራ ፕሮጀክትን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን በሙከራ ደረጃ ለማስጀመር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሔደ ነው።

ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የዓለም አቀፍ ንግዱን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው።

የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በመሠረታዊነት ለመለወጥ በስትራቴጂ ከታቀዱ ጉዳዮች አንዱ ነፃ የንግድ ቀጠና ማቋቋም ሲሆን ሀገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝና የሎጂስቲክስ ምክር ቤት በፕሮግራም ደረጃ ጸድቋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ከተካተተ አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ጥናት ሲካሔድ መቆየቱን ገልፀዋል።

ጥናቱ አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱም በምክር ቤቱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎችን ማቋቋም እንደ አንድ የፖሊሲ ፕሮግራም ተይዟል ብለዋል።

በዚህ መሰረት የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና እንደ ሙከራ ፕሮጀክት በመጽደቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።

ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ ያደርጋል።

በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች አጠቃላይ ንግድ፣ ሁሉን አቀፍ የሎጅስቲክስ አገልግሎትና የአምራች ዘርፉ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብዙ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ እስካሁን የንግድ ቀጠና ባለመኖሩም ህብረተሰቡ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ማስተናገዱን ገልፀዋል።

ጉዳቶቹን መቀነስ ከተቻለ ደግሞ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማስገኘት፤ ነጻ የንግድ ቀጠናውን በሙከራ ደረጃ በአፋጣኝ መመስረት አስፈላጊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በጎረቤት ሃገራት ነጻ የንግድ ቀጠናዎች ያሉ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎችና ሌሎች አካላትን በመሳብ ወደ ነጻ ንግድ ቀጣናው ማስገባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዚህ ፕሮጀክት መሳካት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማሻሻል የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት እንደሚያቀላጥፍ ገልፀዋል።

ለኢንዱስትሪና ከተሞች ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል መስፋፋት፣ ለኑሮ ውድነት መቀነስ፣ በአጠቃላይ ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

ነጻ የንግድ ቀጠናው ወደ ስራ እንዲገባ ባልድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ነጻ የንግድ ቀጠናውን ተግባራዊ ማድረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ በመሳብና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።   

ነጻ የንግድ ቀጠናዎች በአንድ ሃገር ውስጥ ያሉ፣ በብዛት ለወደብ ወይም ለድንበር ቅርብ በሆነ ቦታ የሚገኙ ሆነው፤ ገቢ ዕቃዎች ከጉምሩክ እና ሌሎችም ታክሶች ነጻ ሆነው የሚገቡባቸው የተከለሉ ቦታዎች ናቸው።

ነጻ የንግድ ቀጠናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጠናዎች አካል ሲሆኑ በውስጣቸው እሴት የሚጨምሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የማምረት ሥራዎች፣ እንዲሁም ንግድ የሚከናወንባቸው ናቸው።

በ129 ሃገራት ወደ 5 ሺህ 400 ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ አብዛኞቹ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ነጻ የንግድ ቀጠናዎች በአብዛኛው በእስያ (በዋነኝነት ቻይና እና መካከለኛው ምስራቅ) የሚገኙ ሲሆን፤ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ደግሞ ተከታዩን ደረጃ ይይዛሉ።

የአፍሪካ አገራት ድርሻ ከአምስት በመቶ በታች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም