ህዝቡን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ተሰርቷል-- የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

ሀዋሳ ሰኔ 26/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት አመታት የክልሉን ህዝብ በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ፡፡

የክልሉን 2ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በልማት ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በሃዋሳ እየተካሄደ ነው፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት የክልሉ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ካገኘ ወዲህ በፖለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍም ህዝቡን በልማቱ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በማድረግ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

በመንግስት መሪነትና በህዝቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ በጋራ የሚጠቀምባቸውን የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በቤተሰብ ደረጃ  ኑሮን በሚያሻሽሉ ልማቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከጥቃቅንና አነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ኢንደስትሪዎች ልማት ላይ ከግንዛቤ መፍጠር ባለፈ የመስሪያ ቦታና በጀት በመመደብ በርካታ ሰዎች ተደራጅተው የግል ኑሯቸውን መቀየር በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት በገጠርና በከተሞች ተደራሽ መደረጉን ገልጸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ከህዝብና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መገምገመ  ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በቀጣይ ለመስኖ መሰረተ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው ለውይይት ባቀረቡት ሰነድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የተገኘው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚመለከታቸው አካላት በባለቤትነት መስራት እንዳለበቸውና ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ መጠቀም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የመኢአድ የሲዳማ ክልል ሰብሳቢ አቶ አቻ ለገሰ በበኩላቸው በመንገድ፣ በጤና፣ በውሃ፣ በግብርና በሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እንደተፎካካሪ ፓርቲ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ እንድንሳተፍ እድል መፈጠሩ ቀደም ሲል ያልነበረ የለውጥ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እያከናወነ ያለው የልማት ስራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የነጋዴውን ማህበረሰብ ወክለው የተገኙትና ከሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ የመጡት አቶ ወላንሳ ኤጋሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ተግባራትን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለበርካታ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን ገልፀው አሁን በመጣው ፍጥነት ከቀጠለ በቀጣይ የህዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መፍታት የሚችል አቅሙን ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ክልሉ የተመሰረተበት 2ኛ ዓመትም ነገ ሰኔ 27 ቀን 2014 በክልል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም