ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻችንን እናበረክታለን– የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት መሪዎች

118

ባህርዳር ሰኔ 26/2014 (ኢዜአ) የሀገርን ሰላምና አንድነት ለአደጋ እያጋለጡ ያሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት መሪዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባህርዳር ሃገረ ስብከት የካህናት አገልግሎት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ መላከ ምህረት መምህር ፈለገጥበብ አንዷለም ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ሰላም ዘላቂነትና እድገት ለማስቀጠል ችግሮችን በምክክር መፍታት አስፈላጊ ነው።

ሀገርን ለአደጋ ለማጋለጥ የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሯቸውን ችግሮች ማክሰም የሚቻለው ለህዝቦች አብሮነት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በውይይት መፍታት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ሰላም ካለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ማልማት እንደሚችል ጠቅሰው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምክክር እስከታች ድረስ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።  

“እንኳን በአገር ጉዳይ በግላዊና በአካባቢያዊ ጉዳይ ላይ ከመወሰን በፊት መመካከር፣ መነጋገርና መወያየት አስፈላጊ ነው” ያሉት ደግሞ በክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርትና ዳዕዋ ዘርፍ ሃላፊ ሼህ አህመድ ዘይኑ ናቸው።

አገራዊ የምክክር መድረኩን በስኬት በማጠናቀቅ የአገር አንድነትን ለማጽናት ለሚደረገው ጥረት ህዝብን በማስተማር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አደራው በበኩላቸው የሲቪክ ማህበራት ብሄራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

ማህበራቱ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ህብረተሰቡን በማደራጀትና ግንዛቤውን በማሳደግ፣ የስነ ልቦና ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

የነጋዴ ሴቶች ማህበርም በክልሉ ከሚገኙ ሌሎች የሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር በአገራዊ ምክክሩ የበኩሉን ሚና ለመጫወት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ከደህንነት ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር የሃይማኖት አባቶችን፣ ሲቪክ ማህበራትንና ሌሎች አካላትን ያሳተፈ በብሄራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት ላይ የውይይት መድረክ ማካሄዱን መዘገባችን የሚታወስ ነው።