ችግኝ የምንተክለው ለመጪው ትውልድ የምትመች አገር ለማስረከብ ነው - ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ

231

ሰኔ 26/2014/ኢዜአ/ ችግኝ የምንተክለው ለመጪው ትውልድ የምትመች አገር ለማስረከብ ነው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 'ዐሻራችን ለትውልዳችን በሚል ዘንድሮ የሚካሄደውን አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በፒኮክ መናፈሻ ጀምሯል።

ሚኒስቴሩ ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 የለያቸውን 10 የአቅመ ደካሞች ቤቶችን የማደስ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።  

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ችግኞችን  መትከል  ለመጪው ትውልድ ጥላና በረከት ማኖር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ችግኞችን የምንተክለው ኢትዮጵያን ለልጆቻችን የምትመች ሀገር ለማድረግ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቀደምት አባቶች ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ የቆየ ባሕል እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

የምንተክላቸው ችግኞች ከውበትና ከአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታ ባለፈ ለምግብነት የሚውሉና ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢንጂነር ሀብታሙ አያይዘውም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰዎች ተረጋግተው እንዲኖሩና የተመቸ አካባቢን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ችግኞችን በመትከል ማልማትና ተፋሰሶችን በመጠበቅ የአፈር መሸርሸርን ለመግታት መሆኑንም አስረድተዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ትዕግስት ለገሠ በበኩላቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩም የድርሻውን በማበርከት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም እስከ አሁን ከመቶ ለሚልቁ አቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራትና ችግኞችን መትከልመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም