የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የገቢ አማራጮችን አሟጦ መሰብሰብ ይገባል- አቶ ተስፋዬ ይገዙ

121

ሶዶ ሰኔ 26/2014 (ኢዜአ) በክልሉ ያሉ የገቢ አማራጮችን አሟጦ በመሰብሰብ ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ አስገነዘቡ።

የደቡብ  ክልል ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ ግብር አሰባሰብና በታክስ ህጎች ማስከበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ የስነ ምግባር ጥሰት ፈጽመው የተደረሰባቸው 151 ባለሙያዎች ላይም የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱን ገልጿል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሀገራዊ ወጪዎችን በታክስ ገቢ በመሸፈን የሀገር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል።

ሀገራዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓትን በመገንባት ግብርን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህልን ማዳበር እንደሚገባ የገለጹት ሃላፊው፤ በተለይም ወጪዎችን በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ያላሰለሰ ጥረት መደረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

እያደገ የመጣውን የመሰረተ ልማትና መሰል ግንባታዎች ፍላጎት እንዲሁም የዕድገት መር ዕቅዶች በማሳካት የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ግብርን በፍትሐዊነት መክፈልና ገቢዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ የታክስ ስወራና ማጭበርበር እንዲሁም የሌብነት ችግሮችን በመታገል በማጋለጥና ህጋዊ እርምጃዎች በመውሰድ የጥቂቶች የመክበር አባዜን ለመከላከል ክልሉ ቁርጠኛ አቋም መያዙንም አቶ ተስፋዬ አመላክተዋል። 

የታክስና ሌሎች ህጎችን ማክበር የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ አይተኬ ሚና ያለው መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ ሂደትን ተከትሎ ግብርን በወቅቱ በመክፈል የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው የውስጥ ገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለ ቢመጣም ክልሉ ካለው የገቢ አቅምና አማራጭ አንጻር ስራዎች እንደሚቀሩ ተናግረዋል።

የንግድ ስርዓቱ ያለመዘመን፤ የግንዛቤ ችግርና የሌብነትና ማጭበርበር ችግሮች ደግሞ ከዘርፉ ፈተናዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“በሰሩት ልክ ገቢ የማይከፍሉ ግለሰቦች ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት እየፈፀሙ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል” ያሉት ሃላፊዋ፤ በአንጻሩ ግብርን መክፈል ሀገርን ማልማት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ከማጭበርበርና ግብር ስወራ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የታክስ ወንጀሎችን ለመከላከል እንዲቻልም የታክስ አስተዳደር አተገባበር ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በየዘርፉ የስራ ስነ-ምግባርን የጣሱና ብልሹ አሰራር የታየባቸው ከ151 በላይ የተቋሙ ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ የዲስፕሊን ቅጣት መወሰዱንም ሃላፊዋ ጠቅሰዋል።

በህዝብ ሀብት ላይ የተለያዩ ወንጀሎች ለመስራት በሚሞክሩት ላይ እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ወይዘሮ ዘይቱና አስረድተዋል።

ያለ ደረሰኝ የሚደረግ ግብይትን ለመከላከል ቢሮው ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደረሰኝ በማይሰጡ 35 ግብር ከፋዮች ላይ የንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የደረሰ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ጠቁመዋል።

የታክስ ክፍያን ዲጂታላይዝ በማድረግና በማዘመን የሚጠፋውን የከፋዩን ጊዜና ጉልበት ለማዳን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶችን ለማሳደግ ገቢዎችን አሟጦ ለመሰብሰብ ቢሮው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንዲሁም ህግ የማስከበር ስራዎች የቢሮው የቀጣይ ወሳኝ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ወይዘሮ ዘይቱና አመላክተዋል።

በቢሮው የታክስ ህጎች ዘርፍ ባለሙያ አቶ ይርጋ ሀንዲሶ እንዳሉት የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የፋይናንስ አቅርቦት መሠረታዊ መሆኑን ተከትሎ የታክስ ገቢው በሚገባ ሊሰበሰብ ይገባል ብለዋል።

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገው ውይይት የገቢ አማራጮች በአግባቡ ተጠንተውና ተሰብስበው ለልማት እንዲውሉ ርብርብ  ለማድረግ በመስማማት ተጠናቋል።