መገናኛ ብዙሃን 3ኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የተሳካ እንዲሆን በትብብርና በቅንጅት መስራት አለባቸው

ሰኔ 26 ቀን /2014/ኢዜአ/የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሶስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የተሳካ እንዲሆን በትብብርና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው “የአባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤትና የሕዳሴ ግድብ ተሟጋች ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጸ።

ኡስታዝ ጀማል በሽር ኢዜአ በአዳማ ከተማ ለተቋሙ ጋዜጠኞች እየሰጠ ባለው ሙያዊ ስልጠና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲሰራ የገጠሙትን ፈተናዎችና የተገኙ ስኬቶች ላይ የነበረውን ልምድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች አጋርቷል።

በዚህም ወቅት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሶስተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የተሳካ እንዲሆን በትብብርና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ኡስታዝ ጀማል አስገንዝቧል።

ግድቡን አስመልክቶም በተለያዩ ቋንቋዎች የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብትና ባለቤትነት እንዲገነዘብ የማድረግ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸው አመልክቷል።

ጋዜጠኞች ቁንፅል አጀንዳዎች ላይ ብቻ ተወስነው ራሳቸውን ከማባከን ይልቅ በሰፊው ሀገራዊ እይታ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል።

"ግብፆች የዓባይ ልጆች ነን ብለው ሰፊ ስራና ቅስቀሳ እንደሰሩ ሁሉ እኛም የአባይ ንጉሶች ነን ብለን እየሰራን ነው" ያለው ዑስታዝ ጀማል የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማቱ ተቀናጅተው ኢትዮጵያን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው።

"የነበረኝን ልምድ ለማካፈል የመጣሁትም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያዩን ጥቂት ነገሮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ብዙ እሴቶቻችን ላይ ተሰባስበን አንድ ሆነን በትብብር ለመስራት እንድንችል ነው" ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የሀገሪቷ ሚዲያዎች ተሰባስበው በአንድነት መስራት ከቻሉ በዓባይ ወንዝና በግድቡ ዙሪያ የተሳካ ስራ መስራት እንደሚቻል ተናግሯል።

"የዓባይን ልጅ ከእንግዲህ ውሃ ሊጠማው አይገባም፣ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውሃ ልታጠጣ ይገባል ብለን ልክ እነሱ የዓባይ ልጆች ነን እንደሚሉት እኛ የዓባይ ንጉሶች ነን ብለን በሰፊው መነሳትና በትብብር መስራት ከእኛ ይጠበቃል" ብሏል ኡስታዝ ጀማል።

የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ ባለቤትነት ስለግድቡ ለዓለም አቀፉ ማህበሰብ እያስገነዘብን ነው ያለው ኡስታዝ ጀማል፤ሚዲያዎቻችን በተለያዩ ቋንቋዎች በመስራት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ይበልጥ በማስረዳትና በማስገንዘብ እንዲያግዙን ማድረግ አለብን ነው ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለዓባይ ወንዝ በቂ እውቀት እንዲኖረው ማድረግ የእኛ ድርሻ በመሆኑ በጥናትና ምርምር፣ በቱሪዝምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ማስረዳትና ማሳወቅ አለብን ብሏል።

"ኢትዮጵያን ሊጎዳ የመጣ ማንኛውም ኃይል ላይ ሁላችንም መደራደር የለብንም፣እጅጉን ጠንካራ ሆነን መጀመሪያ የጋራ የሆነች ሀገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር በአንድነት መስራት አለብን "ያለው ኡስታዝ ጀማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም