በጤናው ዘርፍ የሚታዩ የአገልግሎት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ጎንደር፣ ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጤናው ዘርፍ የሚታዩ የአገልግሎት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ተናገሩ።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  281 የህክምና ዶክተሮች፣ ሰብስፔሻሊስቶችና ስፔሻሊስቶችን ዛሬ አስመርቋል።

ሚኒስትር ድኤታው በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በህክምናው ዘርፍ የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል በማፍራት የጎላ ድርሻ እያበረከተ ነው።

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልን ቁጥር ለማሻሻል በተሰራው ስራም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አመልክተው፤ በጤናው ዘርፍ  የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተሰራው ስራም የሀኪሞች፣ነርስ፣ ሚድዋፍና ጤና መኮንን ቁጥርን ጥምረት 10 ነጥብ 3 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም አመልክተዋል።

የተገኘውን ውጤት የበለጠ ለማሳደግም የጤና ፓሊሲ ክለሳ፣የአምስት ዓመት የጤና ዘርፍ የለውጥ እቅድ፣የጤና አገልግሎት የሚመራበት አዋጅ ዝግጅት ስራዎች እየተከናውኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

 በመካከለኛ ደረጃና ከፈተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የሚያገዙ ስራዎች በልዩ ትኩርት እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለሥራዎች ውጤታማነት ተመራቂዎች የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስብዋል።

ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ለማድርግም  ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ  ተሞክሮዎችን በማስፍት ከምን ጊዜውም በላይ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

"የዛሬ ተመራቂዎች በታማኝነትና በቅንነት ህዝባቸውን በማገልገል ለሙያው ያላቸውን ታማኝነት በተግባር ልታረጋግጡ ይገባል" ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ናቸው።

ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን እየስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በህልውና ዘምቻው በአሸባሪው ህወሓት የደረስውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ሳይንሳዊ ጥናት በማካሄድ የችግሩን ስፋት የዓለም ህዝብ እንዲያውቀው መደረጉን ጠቁመዋል።

በጦርነቱ የተጎድ ተቋማትን መልሶ በመገንባትና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን መልሶ በማቋቋም ዩኒቨርስቲው ህዝባዊ ሃላፊነቱን ተውጥቷል ብለዋል።

የህክምና ጥራትንና ተደራሽነትን ከማስፋፋት አንጻርም ዘርፍ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርቲው በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህክምና የትምህርት መስክ ያስተማራቸውን 111 ወንድና 70 ሴት በድምሩ 281ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ያስመረቀው በስብ ስፔሻሊቲ፣በስፔሻሊቲና በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ያስተማራችውን መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርስቲው አመራር፣የማህበረስብ አባላት፣የተመራቂ ቤተስቦችና ሌሎች  እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም