የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለ60 ሺህ 99 ነዋሪዎች ማዕድ አጋራ

227

ሰኔ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 126 ሚሊዮን 207 ሺህ 900 ብር በሆነ ወጪ ለ60 ሺህ 99 ነዋሪዎች ማዕድ አጋራ።

የማዕድ ማጋራቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተካሂዷል።ከዚህ ውስጥ በመስቀል አደባባይ በተከናወነው ስነስርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በልዩ ሁኔታ ለሚደግፏቸው 14 ሺህ ዜጎች በድምሩ 30 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የማእድ ማጋራት ተከናውኗል፡፡

“በከፍተኛ የኑሮ ውድነት በዋናነት የሚጎዳው የድሃው ማህበረሰብ ነው” ያሉት ከንቲባዋ፤ በምርጫ ወቅት ከእናንተው ጋር ለችግራችሁ እንቆማለን፤ ብለን ቃል በገባነው መሰረት ቃላችንን ጠብቀን ከእናንተ ጋር እየዋልን እያደርን ሃብት ከህብረተሰባችን አሰባስበን አጠገባችሁ እየደረስን ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የክረምቱ ሁኔታ የሚፈጥረውን ጫና ለማቃለል እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመው፤ 3 ሺህ 400 መኖርያ ቤት ፈርሶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ዜጎች ለስራ መነቃቃት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የከተማ ግብርና ቦታ መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በስራ እንጂ በእርዳታና በድጋፍ እንዳልሆነ ተናግረው፤ ሁሉም በትጋት በሚሰራው ስራ አገር እንደሚለወጥ አስገንዝበዋል።

የዘላቂ ልማት መሰረቱ ሰላም መሆኑን በመግለጽ፤ አብረን ለሰላም መስራት ይኖርብናል በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

“ሰላማችንን ለማደፍረስ ምንም ነገር ውስጥ የሌለ ሰላማዊ ዜጋችን ጭምር የሚጠቃበት ሁኔታ አጋጥሞናል” ያሉት ከንቲባዋ፤ እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም ይህንን ደጋግሞ መናገር መፍትሄ አይሆንን ነገር ግን ምንጩን አውቀን ማድረቅ ይኖርብናል ብለዋል።

አሁን የምናያቸው የሁላችንም ጠላቶች የማንም ወገኖች አይደሉም በማለት ገልጸው፤ ከውጪም የኢትዮጵያ ሃብት በመበዝበዝ የሚታወቁ አካላት ድህነታችን እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆን፤ ያገር ውስጦቹ ደግሞ በማይገባ መንገድ መጠቀም የለመዱና ህዝብን እያስለቀሱ የራሳቸውን ኪስ ማደለብ የለመዱ ናቸው ብለዋል።

ይህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበትና ኢትዮጵያ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት አስገንዝበዋል።የሰላም ባለቤት እንሁን፤ አካባቢያችንን፤ ማንኛውንም ህገወጥ ነገሮች ስርዓት አልበኝነቶችን በመቆጣጠር በማጋለጥ ለልማት አስተዋፅኦ እናድርግ ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ አቶ አስፋው ተክሌ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ባለፉት ጊዜያት ከ378 ሺህ ሰዎች በላይ ሰዎችን ማእድ በማጋራት ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በጋራ ተካፍሎ ለማሳለፍ ሲሰራ ቆይቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም