የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ወደ ሰላም ድርድር መምጣታቸው በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ አድርጓል - ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

135
አዲስ አበባ  መስከረም 2/2011 የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ወደ ሰላም ድርድር መምጣታቸው በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀ መንበር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 65ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ ዛሬ ተጀምሯል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር ማርዲያት ከተቀናቃኛቸው ዶክተር ሬክ ማቻር ለሀገሪቱ ዜጎች ሰላም በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም የሰላም ድርድር ማድረጋቸው ይታወቃል። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም በተካሄደው ውይይት ሁለቱ ተቀናቃኞች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዚህም "በደቡብ ሱዳን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል" ብለዋል። ለዚህ ሰላም መምጣት የሱዳን ፕሬዘዳንት ኦማር ሃሰን አል በሽር እና የዩጋንዳ ፕሬዘዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ላበርከቱት አስትዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል። በቀጠናው የሰፈነው አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲያድግ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል። የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኒያል ደንግ ኒያል በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ኢጋድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያደረጉት አስተዋፅኦ አድንቀዋል። የደቡብ ሱዳን መንግስት ከተቀናቃኙ ፓርቲ ጋር የሰላም ድርድር ላይ መድረሱ ለሀገሪቱ ዜጎች ሰላም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ስብሰባም የኢጋድ አባል አገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም የኢጋድ አጋር አካላት ተገኝተዋል። ከአፍሪካ አገሮች ሁሉ በዕድሜ አነስተኛ የሆነችው ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ. ከታኅሳስ 2013 ጀምሮ ደም አፋሳሽ በሆነ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የቆየች ሲሆን፣ ይህንን ግጭት ለማስቆም የተለያዩ አካላት በርካታ ጥረቶች ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ከ12 ሚሊየን ህዝቧ1ነጥብ 2 ሚሊየንየሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያቸው ቀያቸው እንዲፈናቀሉም ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም