ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ማጠናከሪያ እንዲውል ይሰራል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

111

ድሬዳዋ፤ ሰኔ24/2014(ኢዜአ)በኢትዮጵያ የተጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በማስፋት ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ማጠናከሪያነት እንዲውል መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት  የወጣቶች  በጎ ፈቃድ በድሬዳዋ የተጀመረ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚሁ መረሃ ግብር  19 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።  

በድሬዳዋ ተገኝተው መረሃ ግብሩን ያስጀመሩት ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፤ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራ  ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሀገሪቱን መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች ለመፍታት እያደረጉት የሚገኙት ተግባራት በውጤት እየታጀበ ይገኛል፡፡

አምና  21 ሚሊዮን ወጣቶች ተሣትፈው 38 ሚሊዮን ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት 40 ቢሊዮን ብር የሚገመት የልማት ስራዎች ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።

ወጣቱ ትናንት ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር የከፈለውን መስዋዕትነት ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

በሀገር ውስጥ የተጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀጣዮቹ ዓመታት በማዘመን ከኢትዮጵያ ውጭ ድንበር ተሻግሮ በአፍሪካ ሀገራት እንዲያብብ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ይህ ጥረት የፓን  አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ትናንት በተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከሚኒስትሯ ጋር ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንዳሉት፤ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የከተማውን ማህበራዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ እያቃለሉ ናቸው፡፡

ዘንድሮ መረሃ ግብርም የአረጋዊያን ቤት ከማደስ ሌላ የአረንጓዴ አሻራ ሥራን እንደሚያጠናክር ነው ያመለከቱት፡፡

ድሬዳዋ በተጀመረው መረሃ ግብር ከተሳተፉት መካከል  ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ወጣት ሁሴን መሐመድ ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ከልማቱ ባሻገር የርስበርስ ፍቅራቸውን በማጎልበትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገር ከፍታ በጋራ እንዲቆሙ ማገዙን ተናግሯል፡፡

ከአማራ ክልል የመጣችው ወጣት ሳምራት ብርሃኑ በበኩሏ፤ በጎ አድራጎትን በተግባር ለማሳየት  በመረሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፈች መሆኗን ገልጻለች።

በድሬዳዋ የተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ከመላው ሀገሪቱ ክልሎች እና ከድሬዳዋ የተውጣጡ ወጣቶች ችግኝ በመትከልና  የችግረኛ አረጋዊያንን ቤቶች የማደስ ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ ፡፡