የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም

88

ሰኔ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ ዛሬ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በወቅታዊ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ “የኛ ጠላቶች ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ በማድረግ የጀመረችውን ልማት ማስተጓጎል ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻና ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሕግ ማስከበርና ሽብርተኝነትን የመከላከል ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝና እርምጃዎቹ ውጤት እየተገኘባቸው ነው ብለዋል።

“በሽብር ቡድኖች” ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶች መክሸፋቸውንና በርካታ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን አመልክተዋል።

መንግስት አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ዘርፍ ስራዎችን መደገፉና ማስተዋወቁን ለማደናቀፍ የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

ይህንን ሁኔታ ከሰላምና ጸጥታ ችግሮች ጋር በማያያዝ የተዛባና ሆን ተብሎ ሰዎችን ለማሳሳት የሚደረግ ዘመቻ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ለዜጎች የልማት ፍላጎት ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግና የልማት ስራዎች መስተጓጎል እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

“አረንጓዴ አሻራ ዛፍ የመትከል ልምምድ አይደለም” ያሉት ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ፤ መርሃ ግብሩ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት የደን መመናመንን “ትርጉም ባለው” መልኩ መቀነሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ ብዝሃ ሕይወት መጥፋትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተጎዳች እንደሆነ መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለነዚህ ፈተናዎች መፍትሔ የሚሆን ነው ብለዋል።

ከአገራዊ ልማት ስራዎች አንዱ ከሆነው የአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።

“መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎችን ዋጋ ማሳጣትና ማጣጣል ተገቢ አይደለም” ነው ያሉት ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ በመግለጫቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም