ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት አሁን ካለበት በአራት እጥፍ ያሳድጋል የተባለ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

123

ሰኔ23/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት አሁን ካለበት በአራት እጥፍ ያሳድጋል የተባለ የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ አደረገ፡፡

የቡና ምርት አጠቃላይ የአገሪቱን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ የሚሸፍንና ለብዙ ዘመናት ለአገር ኢኮኖሚ ዋልታ ሆኖ የቆየ ነው፡፡

ከ25 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መተዳደሪያ የሆነ ዘርፍ ስለመሆኑም ይነገራል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የውጭ የቡና ገበያ ምርት አቅርቦት አሁን ካለበት በአራት እጥፍ ያሳድጋል የተባለ የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር፤ ስትራቴጂው ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የቡና አመራረት ስልትን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት መጨመር፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠርና ማዘመን እንዲሁም የተቋሙን አደረጃጀት እስከ ቀበሌ ድረስ ማደራጀትን ያካትታል ብለዋል።

በመሆኑም በዘርፉ አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶች ይዘረጋሉ፤ በእውቀት እንዲመራ የማድረግ እንዲሁም የተቋማዊ አደረጃጀት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ነው ያሉት።

በዚህም በቀጣይ ዓመታት የቡና የውጭ ንግድ አሁን ካለበት 1 ነጥብ 196 ቢሊየን ዶላር  ገቢ ወደ 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ስለሺ ጌታቸው፤ ስትራቴጂው የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን 470 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ 1 ነጥብ 26 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ ያግዛል ብለዋል።

ያሉትን አቅሞች በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ይህ ስትራቴጅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው   አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች፣ አምራቾችና ላኪዎች ፕሬዝዳንት ዶክተር ሁሴን አምቦ በበኩላቸው፤ ስትራቴጂው የቡና ምርት ጥራትን ማሳደግና የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተሻሻሉ የቡና ምርት ዝርያዎችን በማልማት ለገበያ ማቅረብም የስትራቴጂክ እቅዱ አካል መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም