መንግስት የወሰነው የሰላም አማራጭ እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል-የቀድሞ የፊንላንድ ዲፕሎማት

161

ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት የወሰነው የሰላም አማራጭ እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ እንደሚገባ የቀድሞ የፊንላንድ ዲፕሎማት ተናገሩ።

ዲፕሎማቱ ሕወሓት ካለው ድብቅ ፍላጎት አኳያ የመንግስትን የሠላም አማራጭ ይቀበላል ተብሎ እምነት የሚጣልበት ቡድን እንዳልሆነም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በህዝባዊ እምቢተኝነት ከስልጣኑ የተወገደው አሸባሪው ህወሃት በለውጡ ማግስት ወደ መቀሌ መሽጎ የጦር ጉሰማ በሚያሰማበት ወቅት የፌደራል መንግስቱ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም የሽብር ቡድኑ ለመንግስት የሰላም ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግስት በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ ገብቷል።

የህግ ማስከበር እርምጃው በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ መንግስት የትግራይ አርሶ አደር የእርሻ ስራውን ከስጋት ነጻ ሆኖ እንዲያርስና የክልሉ ህብረተሰብ ወደ መደበኛ እንቅሰቃሴ እንዲመለስ በማሰብ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ እንዲወጣ አድርጓል።

ከዚህም ባለፈ መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተለያዩ ጊዜ በተግባር ቢያሳይም፤አሸባሪው ህወሃት ሁለተኛ ዙር ጦርነት ከፍቶ በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።

መንግስት የሽብር ቡድኑ ላይ በወሰደው እርምጃ ወረራውን በመቀልበስ ለሰብዓዊነት ሲባል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

ከዚህም ባለፈ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ያለውን ፅኑ አቋም የአሸባሪው ሕወሃት አባላትን ከእስር በመፍታት እና አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ በመወሰን ቁርጠኝነቱን አሳይቷል።

ለትግራይ ህዝብ ያልተገደበ የሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመሆን በየብስና በአየር ሰብዓዊ ርዳታዎች እንዲጓጓዙ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ከኢዜአ ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የፊንላንድ ዲፕሎማት ሲሞ ፓርቪያነን መንግስት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት ለሰላም ያለውን ፅኑ አቋም በተለያዩ ጊዜያት በተግባር ቢያሳይም፤ሕወሃት ግን ለሰላማዊ አማራጭ ያለውን ግልጽ አቋም አላንጸባረቀም ይላሉ።

በሕወሃት በኩል ለሰላም ውይይቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ቡድኑ ቀድሞውኑ ትክክለኛ ማንነቱ ሰላማዊ መፍትሄን እንደማይሻ ማረጋገጫዎች እንደሆኑም ነው ዲፕሎማቱ የተናገሩት።

መንግስትን ከሰላማዊ አማራጮች በተጫማሪ ያልተገደበ ሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ቢሆንም፤ቡድኑ ዛሬም ድረስ ሰብዓዊ ርዳታውን እያስተጓጎለ መሆኑን ከሰሞኑ ርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች መቀሌ እንዳያርፉ መከልከሉን ለአብነት አንስተዋል።

በውጭ ሀገራት የሚገኙ ሚዲያዎች ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ከሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹ ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ትርምስ እንዲፈጠር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብነትም በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው ግፍ እንዲፈጸም ኖርዌያዊው ኬቲል ትሮንቮልን ጨምሮ የአሸባሪው ህወሃት አኩይ ዓላማ ተባባሪዎች በቅንጅት ሲሰሩ እንደነበርም አውስተዋል።

በመሆኑም ቡድኑ የሰላም ውይይቱን እንደሚቀበል ቢገልጽ እንኳን ቡድኑ ለቃሉ ተፈጻሚነት እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ ዲፕሎማቱ አትተዋል።

ለሰላም ሂደቱ መሪነት ከአፍሪካ ሕብረት ይልቅ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋኒያንን መምረጡም፤ ቡድኑ ድብቅ ፖለቲካዊ ዓላማውን ለማሳካት ሁልጊዜም የውጭ አገራትን ድጋፍ በመሻት እንደሚንቀሳቀስ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰላማዊ ውይይት የሚደረገውና የሚሰምረው ለውስን የጋራ ፍላጎቶች ስኬት ሲባል እንደሆነ ገልጸው፤ ሆኖም ሕወሃት እምነት የሚጣልበት ባለመሆኑ ጉዳዩን ስኬታማ ይሆናል ለማለት እንደሚከብድ ነው የጠቀሱት።

ሕወሃት ሁልጊዜም ሁከትና ብጥብጥን በፖለቲካ መሳሪያነት የሚጠቀም ቡድን መሆኑን አስታውሰው፤አሁንም ከሰላም ይልቅ ብጥብጥን በአማራጭነት እየተከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

ለክልሉ ነዋሪዎች የሚቀርብ ሰብዓዊ ርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ እንደሚጠቀም ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን የቡድኑን አፍራሽ አካሄድ በቅጡ ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት።

አክለውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰላማዊ አማራጮች ስኬት ከመንግስት ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።