መንግስት በድጎማ የሚያቀርበው ነዳጅ ለህገወጥ ንግድ እንዳይጋለጥ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል

116

ጎንደር ሰኔ 22/2014 (ኢዜአ) መንግስት በድጎማ የሚያቀርበው ነዳጅ በአንዳንድ ህገ-ወጥ ማደያዎች ለአየር በአየር ንግድ እንዳይጋለጥ ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ በጎንደር ከተማ የሚገኙ አሽከርካሪዎችና የትራንሰፖርት ማህበራት አሳሰቡ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከቀጣዩ ሀምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ በሚደረገው የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ማሻሻያ  በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

የከተማው የባጃጆች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አስናቀው እንደተናገሩት በትራንስፖርት ዘርፉ ለተሰማሩ አሽከርካሪዎች መንግስት ተግባራዊ የሚያደርገው የነዳጅ ድጎማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ እንዳይጎዳ የሚያደርግ ነው፡፡

መንግስት በከፍተኛ ድጎማ የሚያቀርበው ነዳጅ ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል በነዳጅ ማደያዎች ላይ ተገቢ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ሊተገብር እንደሚገባ ገልጿል፡፡

አዲሱ የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ማሻሻያ አሰራር በየደረጃው በሚገኙ አካላት በኩል ግልጽ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ አደም ጀማል ናቸው።

በማደያዎች አካባቢ የሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት ህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ በሚፈጽሙ ባለማደያዎች መሆኑን ጠቁመው አዲሱ አሰራር ችግሩን በሚቀርፍ መልኩ ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

“በአንዳንድ ማደያዎች ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ማደያው ላይ ሳይራገፉ አየር በአየር የሚሸጡበት ህገ-ወጥ ተግባር በአዲሱ አሰራር ማስተካከል እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ አየልኝ ሙላት ናቸው፡፡

የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በመድረኩ ያነሱት ችግሮች በአንዳንድ ማደያዎች የሚስተዋሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ አመት ብቻ በከተማው 17 ማደያዎች በህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ተሰማርተው በመገኘታቸው  ክስ ተመስርቶባቸው በህግ መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ አሰራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ የተነሱ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ገልጸው ለነዳጅ ድጎማው ፖሊሲ ተግባራዊነት ሁሉም አካላት ሊተባበር እንደሚገባ ነው ያስታወቁት።

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በቅርቡ ተግባራዊ ለሚደረገው የነዳጅ ድጎማ ፖሊሲ ተፈጻሚነት ከተማ አስተዳደሩ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ለነዳጅ ድጎማው ፖሊሲ ተግባራዊነት ለባለ ማደያዎች፣ ለአሽከርካሪዎችና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

አሰራሩን በጥብቅ ዲስፕሊን ለመምራት የሚያስችል አብይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፤ በአሰራሩ ላይ ህገወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላትን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በአዲሱ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ለመሆን 4ሺህ 511 ባለ ሶስት እግር ታክሲዎችና የከተማ አውቶብሶች መመዝገባቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው ትራንስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አለልኝ አያሌው ናቸው፡፡  

በመድረኩ ላይ የታክሲና የባጃጅ ማህበራት አመራሮችና አባላት ባለ ማደያዎችና የአሽከርካሪ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።