በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄን ለመመለስ እየተሰራ ነው

198

ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)በደቡብ ክልል የህብረተሰቡን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ ተናገሩ።

በክልሉ ጌዴኦ ዞን በ61 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው 45 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድና ድልድይ ግንባታ ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

መሠረተ ልማቶቹን የመረቁት ዶክተር አበባየሁ ታደሰ እንደገለጹት በክልሉ የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

ዘንድሮ በገጠር መንገድና በሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገዶች ከ1 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድና ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ ሰፊ የመሠረተ ልማት ጥያቄ መኖሩን አመልክተው፤ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ ህዝብ የመንግስትን የሰላም ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

የደቡብ ክልል መንገዶች ባለሰልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘብዲዮስ ኤካ በተያዘው ዓመት የዘገዩና የህዝብ እሮሮ ያለባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በተደረገ ጥረት አመርቂ ውጤት መገኝቱን ተናግረዋል።

በተለይ የግንባታ ግብዓት ዋጋ መናርና በአንድ አንድ የክልሉ አከባቢዎች የጽጥታ ችግር በስራቸው ላይ ጫና ቢያሳድርም የውስጥ አቅምን በማስተባበር የአመቱን እቅድ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን ጨምሮ በ495 ሚሊዮን ብር ወጭ 800 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 24 የመንገድ ፕሮጀክቶችና 21 መለስተኛ ድልድዮችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አስረድተዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቀረፍ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአገልግሎት የበቁት ሁለት የመንገድና አንድ የድልድይ ግንባታ በዞኑ የአራት ወረዳዎችን የትራንስፖርት አገልግሎት በማቀላጠፍ የህብረተሰቡን ድካምና እንግልት እንደሚቀንሰም ገልጸዋል።

መንገዶቹ ረጅም አመት አገልግሎት እንዲሰጡም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በቂ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ በእለት የእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና ሲያሳደር መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የራጴ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት ብርሃኑ ናቸው።

የመንገዱና ድልድዩ መገንባት የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለንግድ እንቅስቃሴና ነፍሰጡር እናቶችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ እገዛው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአከባቢው ነዋሪ ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም