ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተዘግተው የቆዩ ኢንደስትሪዎች ስራ እንዲጀምሩ እድል እየፈጠረ ነው–ቢሮው

144

ሀዋሳ ሰኔ 22/2014 (ኢዜአ) በክልሉ በተካሄደው “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” በተለያየ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ ኢንደስትሪዎች ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ባለፉት 11 ወራት በመካከለኛ ደረጃ  ላይ ባሉ ኢንዱስትሪዎች ከ20 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ተመላክቷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አሻግሬ ጀንበሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የኮረና ወረርሽኝ፣ የሰላምና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በተፈጠረው መቀዛቀዝ በክልሉ 34 ኢንዱስትሪዎች ከስራ ውጪ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በቅርቡ እንደ ሀገር የተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ በክልሉ ተዘግተው የቆዩ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዲጀምሩ እድል መፍጠሩን ነው ያስታወቁት።

አቶ አሻግሬ እንዳሉት የኤሌትሪክ ሃይል አቅም ማነስ፣ የመስሪያ ቦታ ጥበት፣ የግብዓት እጥረትና የማሽነሪ አቅርቦት ከነበሩ ችግሮች መካከል እንደነበሩ ጠቅሰው ከንቅናቄው በኋላ ችግሮቹን በማቃለል እስካሁን 13ቱ ኢንዱስትሪዎች  ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ገብተዋል።

ስራ ከጀመሩት ውስጥ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ምክንያት ቆመው የነበሩ የብስኩት ማምረቻ፣  የማእድ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ችግር የገጠማቸውን ኢንዱስትሪዎችን ወደስራ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪዎቹን የግብዓት ችግር ለመፍታት አርሶ አደሩን ከመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሃላፊው እንዳሉት ባለፉት 11 ወራት በመካከለኛ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል  መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ስራ ከጀመሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል በ73 ሚሊየን ብር ካፒታል የተቋቋመው ማእድ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሊያ በለጠ ናቸው።

መንግስት ባመቻቸላቸው የብድርና የማምረቻ ቦታ አቅርቦት በክልሉ በብስኩት ማምረት ዘርፍ ቢሰማሩም በመብራት ሃይል ማነስ ምክንያት ስራ ሳይጀምር መቆየቱን ገልጸው በቅርቡ ችግሩ ተቀርፎ ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ 1 ሺ 500 ካርቶን ብስኩት እያመረተ እንደሚገኝና በሙሉ አቅሙ ወደስራ ሲገባ  በቀን እስከ 5 ሺህ ካርቶን የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ፋብሪካው  ለ60  ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩንም ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የአሮማ ፉድ ስታፍ ኢንደስትሪ ስራ አስኪያጅ አቶ አስፋው ሰኢድ በበኩላቸው  ኢንደስትሪው ለምግብና ለመዋቢያነት የሚያገለግሉ የአቡካዶ ዘይት ምርቶችን በማዘጋጀት ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

የአቡካዶ ምርትን ከአምራች የአርሶ አደሮች ህብረት ስራ ማህበር በመግዛት በዓመት እስከ 174 ሺህ ሊትር የአቡካዶ ዘይት እንደሚያመርት ነው የገለጹት፡፡

የማምረት አቅማቸውን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ የቦታ ጥበት መኖሩን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ችግሩ እንዲፈታላቸው ለክልሉ መንግስት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል ከሚገኙ 850 በላይ ኢንዱስትሪዎች መካከል 56ቱ ከፍተኛ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ መካከለኛና አነስተኛ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።