ኢትዮጵያና ሱዳን ያለ ውጫዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት ያሉባቸውን ችግሮች የመፍታት አቅም አላቸው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

101

ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያና ሱዳን ያለ ውጫዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት ያሉባቸውን ችግሮች የመፍታት አቅም አላቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ሁለቱ አገራት የሚያዋጣቸው ልማትና በጋራ ማደግ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ብዙ ችግሮች ቢኖሩም አገራቱ መፍትሄ ለማምጣት በትብብር መንፈስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መንግስታት ወይም ሌሎች” ያሏቸውን ጨምሮ “ብዙዎች”ሁለቱ አገራት እርስ በእርሳቸው እንዲጋጩ ይፈልጋሉ፤ነገር ግን ከግጭት የሚገኝ ምንም አይነት ትርፍ እንደሌለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ የአገራቱና ሕዝቦቹ መካከል ሰላምና የጋራ መተማመን እንዲፈጠር ነው ብለዋል።

በውጭ ጫናዎች ምክንያት ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት መግባት እንደሌለባቸው አመልክተዋል።

ሁለቱ አገራት በመልካም ጉርብትና መርሆች እንዲሁም ለጋራ ፍላጎቶቻቸው ሲሉ በችግሮቻቸው ላይ በሰከነ መንገድ በመወያየት መፍትሔ ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአገራቱ መካከል ምንም አይነት “ጠላትነት ሊኖር አይገባም” የሚበጀው ሁለቱ አገራት የሚያወጣቸው ልማትና በጋራ ማደግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ወንድማማች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ለሱዳናውያን አክብሮት አለን ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ያለ ውጫዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት ያሉባቸውን ችግሮችና ፈተናዎች በወንድማማችነትና በመልካም ጉርብትና መንፈስ የመፍታት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም