ዘላቂ ሠላም ማስፈን የምንችለው በአብሮነት ስንቆም ነው- አቶ አደም ፋራህ

185

ሐዋሳ፤ ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪ ቡድኖችን በመመከት ዘላቂ ሠላምን ማስፈን የምንችለው በአብሮነት ስንቆም ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።

የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አንደኛ ጉባኤ “የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው ።

በጉባኤው  በክብር እንግድነት የተገኙት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በፓርቲው አቅጣጫና በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው  ''በጋራ ጠላቶቻችንን ላይ በማተኮር በሕግ ማስከበሩም ሆነ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋሙ ረገድም ሁለም አካል በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሊሳተፍ  ይገባል'' ብለዋል።

ከአሸባሪው ህወሓትና ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተልዕኮ ወስደው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድንኖች  ኢትዮጵያን ለማዳከም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አመላክተዋል።

 የጥፋት ቡድኖች በአንድ በኩል የታላቁ ህዳሴ ግድብ 3ተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና  በሌላ በኩል ደግሞ እየጎለበተ የመጣውን የህዝቦች አንድነት ለመሸርሸር እኩይ አላማ እንግበው እየተንቀሰቀሱ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ሴራውን  ለማክሸፍ መንግስት የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ተስፋ የቆረጡ የጥፋት መልእክተኞች በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ  ወረዳ  እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ የንፁሀንን ሕይወት መቅጠፋቸውን ተናግረዋል።

''ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ አሸባሪ  ቡድኖች ሥርዓት ማስያዝና ዘላቂ ሠላም ማስፈን የምንችለው በአብሮነት ስንቆም ነው'' ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤  እርስ በርስ ጣት ከመቀሳሰር ይልቅ በጋራ ጠላቶቻችንን ላይ በማተኮር በሕግ ማስከበሩም ሆነ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋሙ ሥራ ላይ  በአንድነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ   በቅርቡ ባደረጓቸው ስብሰባዎች ድርጊቱን ማውገዛቸውንና የሕግ ማስከበር ዘመቻው  ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ጠቁመዋል።

አቅጣጫውን ተከትሎ   በተከናወነው ሥራም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውና በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

አካባቢውን ከሽብርተኞች ነፃ በማድረግ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም ከመላው ኢትዮጵያዊያንና ከሚመለከታቸው አካላት አካላት ጋር  በመሆን የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም