አንጋፋው ደራሲና ጸሐፈ-ተውኔት ሠለሞን ዓለሙ በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት ትልቅ አሻራ አስቀምጧል-የሙያ ባልደረቦቹ

208

ሰኔ 22/2014/ኢዜአ አንጋፋው ደራሲና ጸሐፈ-ተውኔት ሠለሞን ዓለሙ በስራዎቹ ትውልድን ከማስተማር ባሻገር በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በማፍራት ትልቅ አሻራ ያሳረፈ የኪነ ጥበብ ሰው መሆኑን የሙያ ባልደረቦቹ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የራሱን ደማቅ አሻራ የነበረው አንጋፋው የኪነ ጥበብ ሰው ሠለሞን ዓለሙ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉት ከ500 በላይ የሬዲዮ ድራማዎችን፣ የመድረክ ቴአትሮችን እና መነባንቦችን ደርሷል።

ከአንድ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የተላለፈው 'የሸምጋይ' ተከታታይ ድራማን ጨምሮ ከዳንኪራው ጀርባ፣ ፍራሽ ሜዳ፣ ግርዶሽ፣ ገመዱ፣ ድብልቅልቅ፣ በድሉ ግራኙ፣ አዙሪትና ፅናት ከስራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

ደራሲና ፀሐፈ-ተውኔት ሰለሞን አለሙ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በተወለደ በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የባለሙያው ስርዓተ ቀብርም የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች እና የሙያ አድናቂዎቹ በተገኙበት ከሰዓት በኋላ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከናውኗል።

ከስርዓተ ቀብሩ ቀደም ብሎም በብሔራዊ ቴአትር የአስከሬን ሽንት መርሐ ግብር ተደርጓል።

የባለታሪኩ የቅርብ ጓደኛ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ፤ ሠሎሞን ዓለሙ የሬዲዮ ድራማን ከፍ ባለ ሁኔታ ያስተዋወቀ መሆኑን ገልጾ፤ ለአብነትም "ሸምጋይ" ወይም "አብዬ ዘርጋው" የሬዲዮ ድራማዎችን ጠቅሷል።

ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ጽሑፎችም ወጣቱን ትውልድ በማስተማርና በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልጿል።

"አፍለኛው" የተሰኘ የቴአትር ቡድን የመሰረተው ባለታሪኩ፤ ከፀሐፈ ተውኔትነቱ ባሻገር የቴአትር  ሙያተኞችን በማፍራት፣ የባለሙያዎችን ሥነ-ምግባር በመቅረፅ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን አስታውሷል።

የረዥም ጊዜ የሙያ አጋሩ ተዋናይት ድርብወርቅ ሰይፉ፤ ሠለሞን አለሙ በርካታ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን ማፍራቱን ገልጻለች።

በተለይም 'አፍለኛው' በተሰኘው የሬዲዮ ድራማ በርካታ ወጣት ባለሙያዎችን ለህዝብ ማስተዋወቁን አስታውሳለች።

ባለሙያው ሙያውን አክባሪነቱ ለሌሎችም ባለሙያዎች በአርዓያነቱ እንደሚጠቀስ ምስክርነቷን ሰጥታ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ የኪነ ጥበብ ሰው ማጣቷን ነው የገለጸችው።

ደራሲና ጸሐፊ ተውኔት ሠለሞን ዓለሙ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም