የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የጀርመን ልማት ባንክ የ32 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

115

ሰኔ 22/2014/ኢዜአ/ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የጀርመን ልማት ባንክ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችን የሰው ኃይል ልማት ትስስር የሚያጠናክር የ32 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል ።

ድጋፉ በአራት ክልሎች የሚገኙ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በጋራ የተግባር ስልጠና እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት፤ የጀርመን ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማጠናከር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለትም የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችልና በተለይም በኢንዱስትሪዎችና በሰለጠነ የሰው ኃይሉ መካከል ትስስር የሚፈጥር ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት የጀርመን ልማት ባንክ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ውጤታማ ለማድረግና ከኢንዱስትሪው ጋር በሰው ኃይል ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር የ32 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።

ድጋፉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል። በተያያዘ መረጃ የጀርመን ልማት ባንክና የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 20 የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ወደ ዲጂታላይዜሽን ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱን በቁሳቁስ ለማጠናከር ብሎም ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።

የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ክሪስቶፍ ቲስከንስ በበኩላቸው ባንኩ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መርሃ ግብሮች የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ሲደግፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን ለዘርፉ ከ200 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ባንኩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።