የጋዜጠኛ ኃይለ ሚካኤል ዋሴ የቀብር ስነ ስርአት ተፈጸመ

173

ሰኔ 22/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለረጅም ዓመታት ያገለገለው የጋዜጠኛ ኃይለ ሚካኤል ዋሴ የቀብር ስነ ስርአት ተፈጸመ።

ጋዜጠኛ ኃይለ ሚካኤል ዋሴ ከእናቱ ወይዘሮ ብዙነሽ ዳዲ ከአባቱ አቶ ዋሴ መብራቱ ሚያዚያ 12 ቀን 1949 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 13 አካባቢ ተወለደ።  

ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ከ1 እስከ   12ኛ ክፍል በአዲስ አበባ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች   እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርቱን በቀድሞ የመገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተከታትሏል።

በሀገር ውስጥ ከጋዜጠኝነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን ፤በውጭ ደግሞ በጀርመን በርሊን ለአምስት ሳምንታት በሙያው ዙሪያ ስልጠና  መውሰዱን ከህይወት ታሪኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በስራ ዓለም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ውስጥ አንደኛ ደረጃ ዋና ወኪል በመሆን መስከረም 7 ቀን 1972ዓ.ም ተቀጠረ።

በኢዜአ በቆየባቸው ዓመታት በተለያዩ  ቅርንጫፎች  ተዘዋውሮ  በጋዜጠኝነት ሙያና ኃላፊነት  ካገለገለባቸው መካከል  አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣  አሰላ ፣ ሐረርና  አሰብ  ይገኙበታል።

ወደ ዋናው መስሪያ ቤት አዲስ አበባ በመዛወርም  ጡረታ ከወጣበት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ የሀገር ውስጥ ዜና ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ በዜና አርታኢነት ሰርቷል።

ጋዜጠኛ ኃይለሚካኤል ዋሴ በስራ ዓለም በቆየባቸው ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ታታሪ፤  በማህበራዊ ህይወቱም  ተግባቢ ፣ ቅን፣ ሩህሩህና መልካም ግንኙነት   እንደነበረው ጓደኞቹና የስራ ባልደረቦቹ ይመሰክራሉ።

ጋዜጠኛ ኃይለሚካኤል በድንገተኛ ሁኔታ  ሰኔ 21ቀን 2014ዓ.ም በ65 ዓመቱ  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ባለትዳርና የሶስት ወንዶች ልጆች አባት የነበረው ጋዜጠኛ ኃይለሚካኤ ዋሴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2014ዓ.ም በአዲስ አበባ ልደታ ማሪያም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

ባልደረቦቹና ጓደኞቹ በጋዜጠኛ ኃይለሚካኤል ዋሴ መብራቱ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጹ ፤ለቤተሰቦቹ እንዲሁም ዘመድ ወዳጆቹ መፅናናትን ተመኝተዋል።