አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የፍትሐዊነትና የአካታችነት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው-የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ

120

ባህር ዳር፣ ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) “አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ የሚሆነው በየዘመኑ ሲነሱ የቆዩ የፍትሐዊነትና የአካታችነት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ሲችል ነው” ሲሉ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ከደህንነት ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ''አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ አስፈላጊነት የባለድርሻ አካላት ሚና እና የቢሆን ትንተናዎች'' በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዚህ ወቅት “ለዘመናት የዘለቀ መንግስታዊ ስርዓት ከገነቡ ውስን አገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ጠንካራ አገረ መንግስት ተገንብቷል” ብለዋል።

ይሁንና በአገረ መንግስት ግንባታው ላይ በብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ጉዳዮች የአካታችነትና የፍትሐዊነት ጥያቄዎች በየዘመኑ ሲነሱ እንደቆዩ ገልጸዋል።

በየጊዜው የሚነሱ የአካታችነትና ፍትሐዊነት ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ እንደሚያደርገውና ጠንካራ አገር መገንባት እንደሚቻል ነው የገለጹት።

ምሁራን የምክክር መድረኩ የታለመትን አላማ እንዲያሳካ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ዶክተር ፍሬው ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ አገራዊ ምክክሩን የተመለከቱ የመነሻ ጽሁፎች በምሁራን የቀረበ ሲሆን በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር የሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም