የአውራ አምባ ማህበረሰብ ወገንተኝነትን የማስወገድ መርሕ ለኢትዮጵያም የሚያገልግል መሆን አለበት- የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ

236

ሰኔ 21 ቀን 2014(ኢዜአ) "የአውራ አምባ ማህበረሰብ የወገንተኝነት ማስወገድ መርሕ ለኢትዮጵያም ጭምር የሚያገለግል መሆን አለበት" ሲሉ የማህበረሰቡ መስራች የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ገለጹ።

የአውራ አምባ ማህበረሰብ 50ኛ ዓመትን በማስመልከት "ዙምራ" የሚል መጽሐፍና ዘጋቢ ፊልም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ተምርቋል።

መጽሐፉ የማህበረሰቡን የግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን በዶክተር ዘካርያ ዓምደብርሃን፣ በዶክተር ክንድዓለም ዳምጤና በጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተጽፏል።

የዘጋቢ ፊልሙ ደግሞ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለእይታ በቅቷል።

የአውራ አምባ ማኅበረሰብ መሥራች የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ "የአውራ አምባ ማኅበረሰብ ለዓመታት ያለምንም መከፋፈል አንድ ሆኖ ኖሯል።

"ይህም ወገንተኝነትንና ከፋፋይ አስተሳሰብን በማስወገድ ኢትዮጵያን በትብብር መገንባት እንዳለብን ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የአውራ አምባ ማህበረሰብ የሕጻናት መብትን መጠበቅ፣ የጾታ እኩልነትን ማክበር፣ አቅመ ደካሞችና አረጋውያንን መርዳትና መጥፎ ከመናገርና ከመሥራት መቆጠብ የሚሉ መርሆች እንዳሉት ገልጸዋል።

ዋንኛ የማህበረሰቡ መርሕ የሆነው ወገንተኝነትን ማስወገድ ለኢትዮጵያም ጭምር የሚያገልግልህ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ከአውራ አምባ ማህበረሰብ በመማር ለሌሎች ሰዎች ሕይወት መቀየር ምን ያህል ምክንያት ሆነናል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንዳለብን ያሳያል ብለዋል።

የአውራ አምባ ማህበረሰብ አኗኗር ለውጥ ከቤተሰብ፣ ከመንደርና ከአካባቢ መነሳት እንዲሁም ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረቀውም መጽሐፍ ለትውልዱ ማስተማሪያ እንዲሆን በሥርዓተ ትምህርት በማካተት ጭምር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የዙምራ መጽሐፍ 417 ገጾች ያሉትና በአስር ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን ዘጋቢ ፊልሙ ደግሞ የአንድ ሰዓት ርዝማኔ አለው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም