የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለ2015 በጀት ዓመት የ100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር የበጀት እቅዱ እንዲፀድቅ ለከተማው ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳለፈ

152

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለ2015 በጀት ዓመት የ100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር የበጀት እቅዱ እንዲፀድቅ ለከተማው ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል።

ካቢኔው ዛሬ ከአረንጓዴ አሻራ ማስጀመርያ መርሃ-ግብር መልስ ባካሄደው የ1ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰበው በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ከ2015 እስከ 2017 ዓመታትን ባካተተው የወጪ ማዕቀፍ ዕቅዱ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ ለ2015 በጀት ዓመት በከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር በጀትን ተቀብሎ በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከተወሰነው በጀት ውስጥ 29 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ለክፍለ ከተሞች በድጎማ መልክ የሚሰጥ ሲሆን፥ ቀሪው 70 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ደግሞ በከተማው በማዕከል ደረጃ ለአስፈጻሚ አካላት የተበጀተ ነው፡፡

ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት ነው፡፡

ከተበጀተው 70 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ውስጥ 54 ነጥብ 87 በመቶዉ የካፒታል በጀት ሲሆን 42.29 በመቶዉ ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎች የሚውል ነው፡፡

ቀሪው 3.87 በመቶ በመጠባበቂያነት የተያዘ በጀት መሆኑ በበጀት እቅዱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ ግቦችን ዉጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት (Infrastructure); ለፈጠራ (Innovation) እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በመደልደል ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም