ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

130

ጂንካ፤ ሰኔ 21/2014(ኢዜአ)፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኦሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና 3 ስኳር ፕሮጀክት በጂንካና አከባቢዋ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።

 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኦሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት ለተጎጅዎቹ ዛሬ የተሰጡት ብርድ ልብስ፣ ምንጣፍ ፣ የንፅህና መጠበቂያና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን ከጀርመን ቀይ መስቀል ማህበር በተገኘ 3 ሚሊዮን ብር የተገዙ  ናቸው።

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 290 አባወራዎችና 1 ሺህ 500 ቤተሰቦቻቸው በድጋፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጸጥታ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ  በአራት ዙር አባላቱንና ሌሎችንም አካላት በማስተባበር ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእለት ደራሽ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና 3 ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ሰራተኞች፣ በፕሮጀክቱ አከባቢ የሚሰሩ አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራትንና ሌሎችንም ተቋማት በማስተባበር የ200 ሺህ ብር የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉ 12 ኩንታል ስኳርና 19 ኩንታል የጤፍ ዱቀት መሆኑን ጠቁመው፤ ”የተቸገሩ ወገኖቻችን መርዳት እራስን መርዳት ስለሆነ ሁሉም የአቅሙን ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።

 በቀጣይም ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ የፕሮጀክቱ ሰራተኞችና አመራሩ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ተጠሪ አቶ ተካልኝ ጋሎ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ማህበሩም ሆነ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ግብረ ሃይሉ ሃብት በማሰባሰብ በጉዳቱ ሳቢያ የወደሙትን ከ147 በላይ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የመልሶ ማቋቋም ግብር ሃይል አባልና የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ  ናቸው።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር የ80 ቤቶችን ግንባታ ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ቀሪዎችን ቤቶች  በማጠናቀቅ ለተጎጂዎቹ ለማስረከብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከድጋፉ ተጠቃሚዎች  መካከል በደቡብ አሪ ወረዳ የቶልታ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ  ላቀች በየነ በሰጡት አስተያየት  ከጎናቸው ሆነው ለደገፏቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ደቡብ ኦሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ተጎጂዎች ድጋፍ ሲያደርግ  የአሁኑ ለ5ኛ ጊዜ  መሆኑ ተመላክቷል።