በኢንተርፕራይዞች ተዘጋጅተው ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 24 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

162

ሀዋሳ፤ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ)፡- ባለፉት አስር ወራት በጥቃንቅንና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተዘጋጅተው ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 24 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡

ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የዘርፉ  ባለሙያዎች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ  እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት  ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ብሩ ወልዴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘርፉ ካለው እምቅ ሃብት አንጻር በበቂ ሁኔታ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን በመፍጠር በአለም ገበያ ውስጥ መግባትና የኤክስፖርት መጠኑን ማሳደግ በቀጣይ በትኩረት የሚከናወን ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በሃገር ደረጃ የተጀመረው የ"ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የውጭ ንግድ መጠኑን ለማሳደግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ንቅናቄው በተለያዩ ምክንያት የተዘጉ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ስራ ለማስጀመር ማስቻሉን ገልጸው፤  ዘርፉን በተገቢው መደገፍ የሃገር ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ነው ያስረዱት፡፡

ባለፉት 10 ወራት በሃገሪቱ ካሉ ኢንተርፕራይዞች ተዘጋጅተው  ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 24 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች እንጀራን ጨምሮ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፉ ከፍተኛ ሲሆን ጨርቃጨርቅና ቅመማቅመም እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡

ገቢው ካለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ ቢሆንም ካደጉት ሃገራት አንጻር ብዙ ይቀረናል ያሉት ዋና  ዳይሬክተሩ ፤ እንደሃገር ወደ ውጭ መላክ የሚስችሉ  በርካታ ምርቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች በየአካባቢያቸው ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር በመፍጠርና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን በማጎልበት  ገቢውን ማሳደግ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው በቀጣዩ ዓመት ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ዘርፉን የሚደግፉ ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ የሚረዳ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ከኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ የመጡት አቶ ገመቺስ ተስፋዬ ፤በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና ሃብቱን ለመጠቀም መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ፣ በዘይትና በአበባ ምርት ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በከተማው መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቂ ድጋፍ በማድረግ ወደ ውጭ የመላክ  አቅማቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ቅመማ ቅመምና ቡናን ጨምሮ ከፍተኛ ሃብት በአካባቢው መኖሩን የተናገሩት ደግሞ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የተወከሉት አቶ ስዩም ተፈራ ናቸው፡፡

የየአካባቢውን ምርት ገበያው በሚፈልገው ልክ ለማምረት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ስልጠናው ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ፣እንደ ሃገር ባሉ የዘርፉ ዕድሎችና የድጋፍ ማዕቀፎችን ጨምሮ ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለሶስት ቀናት እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

በዚህም ከ300 በላይ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እንደሚኖር ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም