የተቀዛቀዘውን ንግድ ለማነቃቃት የንግድ ማህበራት ዘመኑ የሚጠይቀውን አደረጃጀት እንዲፈጥሩ እየተሰራ ነው

135

ሰኔ 21/2014 /ኢዜአ/ በዓለም አቀፋዊና ውስጣዊ ጫናዎች የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ በአዲስ መንፈስ ለማነቃቃት የንግድ ማህበራት ዘመኑ የሚጠይቀው ቁመናና አደረጃጀት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ተናገሩ፡፡

ወይዘሮ መሰንበት ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት በዓል ዛሬ በተለያዩ ዝግጀቶች ባከበረበት ወቅት ነው።

በ1939 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በቻርተር የተመሰረተው የአዲስ አበባ ንግድ ማህበራት ምክር ቤት በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ መካከል አገናኝ ድልድይ ሆኖ ለመስራት የተቋቋመ ነው።

በዓሉ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ለሀገር ውስጥ ገበያና ለዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች የሚያቀርቧቸው ምርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለመስራት ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል ወይዘሮ መሰንበት።

በአሁኑ ወቅትም የግሉን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል እና የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን በትጋት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዘመኑን የሚመጥኑ አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ኃሳቦችን በማቅረብና የመፍትሔ አካል በመሆን የሚያጋጥሙ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሚናውን ይወጣል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚኝ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የንግድ እንቅሰቃሴ በዓለም አቀፍና በውስጣዊ ጫናዎች መቀዛቀዝ እንደሚታይበት ገልጸው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የተቀዛቀዘውን የንግድ ልውውጥና የስራ ተነሳሽነት በአዲስ መንፈስ ለማነቃቃት ምክር ቤቱ የበኩሉን እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ።

ለዚህም ፈተናዎችን በመቋቋም ለሀገር አለኝታ የሚሆን የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠርና በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ቁልፍ ሚና ለመጫወት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የንግድ ማህበራትም ዘመኑ የሚጠይቀውን አሻጋሪ የተቋም አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖራቸው እንቅሰቃሴ መጀመሩንም በማንሳት።

የምክር ቤቱ 75ኛ ዓመት በዓሉ እስከ ሰኔ 23 ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የምክር ቤቱን ጉዞ የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ሲቀርብ የ75 ዓመት ታሪኩን የያዘ መፅሐፍም ተመርቋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተለያዩ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና የንግዱ ዘርፍ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የፎቶ አውደ ርዕይም ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም