አገራዊ የምክክር ለማሳካት የድርሻዬን እወጣለሁ... የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

152

አዲስ አበባ ሰኔ 21 ቀን 2014(ኢዜአ) አገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ።

ሁለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከሰኔ 23 እስከ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የስራ ሃላፊዎች ሁለተኛው ማህበረሰብ ድርጅቶች  ሳምንት አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ባለስልጣኑ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ህብረተሰቡ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠርና የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች  ሳምንት "ንቁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ እና ለልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል ብለዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር የጀመሩትን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር የሚዘጋጀው ኩነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መረሀ ግብሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማናቸውም እንቅስቃሴ ያላቸውን ሚና ለህብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ለብሔራዊ መግባባት፣ የልማትና እድገት እንዲሁም ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያግዙ አስገንዝበዋል።

በተለይ የብሔራዊ ምክክሩ ሂደት አካታችና ግልጸኝነትን የተላበሰ እንዲሆን የማገዝ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

መብትና ግዴታውን በውል የተረዳ፣ በውይይትና በምክንያታዊነት የሚያምን፣ የነቃና በነጻነት የተደራጀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ፤ ፕሮግራሙ ድርጅቶቹ ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በመርሀ ግብሩ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽን እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ፣ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ የሀሳብ መለዋወጫ መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ 3700 በላይ የሲቪል ማህበረሰቦች አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም