በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

78

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ) ባለፉት 11 ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የ2014/15 የስራ  ዘመን የደረጃ “ሐ”፣ “ለ” እና “ሀ” ግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ በንቅናቄ መድረኩ እንዳሉት፤  በበጀት ዓመቱ   11 ወራት የተሰበሰበ ገቢ የዕቅዱን  ከ99 በመቶ በላይ  ያሳካ ነው።

ክልሉ ያለውን የገቢ አቅም አሟጦ በመሰብሰብ የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ቢሮው  አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጪው በጀት ዓመትም ይህንን ስራ በማጠናከር   4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ዕቅዱን ለማሳካት የንቅናቄ ሥራው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በማውረድ  በቅንጅት ለመስራት ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ፤ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ከሌብነት በፀዳ መልኩ በየደረጃው እንዲፈጸም የክልሉ መንግስት ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኘውን ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚህ እውን መሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ሊንቀሰቀሱና በቅርበት እንዲደግፉ አቶ ፀጋዬ ጥሪ አቅርበዋል።

በንቅናቄው መድረክ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና የንግዱ ማግበረሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ የምዕራብ ኦሞ፣ ፣ ቤንች ሸኮ ፣ ካፋ ዞን፣ ዳውሮና  ሸካ ዞኖች  እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦች በህዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል ለመደራጀት መወሰናቸውን ተከትሎ  ከተመሰረተ ስምንት ወራት ማስቆጠሩ ይታወሳል።