በህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ጥፋተኛ የተባሉ 77 ሰዎች በእስራት ተቀጡ

150

መተማ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፉት 11 ወራት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ 77 ግለሰቦች እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ኢብራሂም የሱፍ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዞኑ በከፍተኛ ደረጃ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በመሻገር የሚወጡበት አካባቢ ነው።

"በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሰዎች መነገድ ወንጀል የሚሳተፉ ግለሰቦችን በተቀናጀ መንገድ ለህግ በማቅረብ ባለፉት 11 ወራት የተሻለ ስራ ማከናወን ተችሏል"ብለዋል።

በወንጀሉ ተጠርጥረው በ22 መዝገቦች ክስ የተመሰረተባቸውና ጥፋተኝነታቸው በቀረበ የሰውና የሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠ 77 ግለሰቦች በፅኑ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 3 መሰረት ከሶስት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን አስታውቀዋል።

ወንጀሉን በመከላከልም ሆነ ወንጀለኞች እንዲቀጡ በማድረግ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የግጭት አፈታትና የሰላም እሴቶች ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ጋዲሳ በበኩላቸው "ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ሊደርስባቸው ከሚችል ሰብዓዊ፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የግንዛቤ በመፍጠር ህዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት በዚህ አመት 3 ሺህ 100 የሚጠጉ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ሊሻገሩ ሲሉ ተይዘው ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ግዛቸው አስማማው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በቀጣይም ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል ።

በሰዎች ላይ የሚደረግ ንግድን ማስቆም የመላው ህዝብ ሃላፊነት በመሆኑ ለምዕመናን ተገቢውን ግንዛቤ በመስጠት ድርጊቱን ለመከላከል የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የምድረገነት ከተማ ነዋሪ ቄስ ረዳ ደምለው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም