ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚጠበቅብንን እናበረክታለን

94

ባህር ዳር ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ) ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ በጎንደር ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ። 

የጎንደር ከተማ የጊዎን እርቀ ሰላምና ልማት ማህበር የሽማግሌዎች አባል መልዓከ ስብሃት ሞገስ ዓለሙ እንዳሉት የሀገር ዘላቂ የሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል።

አርሶ ለመብላት፣ ወጥቶ ለመግባት፣ ነግዶ ለማትረፍም ሆነ እምነትን ለማረማድ ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል።

በጎንደር ከተማ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረው ችግር በሰከነ፣ በተረጋጋና በመደማመጥ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተማው ይስታዋል የነበረውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር ስራ ስርአት መያዙን ጠቅሰዋል።

''ሰላም ከራስ ይጀምራል ከዚያም ለጎረቤት ከዚያም ለሃገር'' ያሉት መልዓከ ስብሃት ሞገስ ለዚህም ሁሉም ለሰላም መስፈን ዘብ ሊቆም እንደሚገባ ገልጸው እሳቸውም ምዕምናኑን በማስተማር የድርሻችን እንደሚወጡ  ተናግረዋል። 

የጎንደር ከተማ የሰላም አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢና የጊዎን እርቀ ሰላምና ልማት ማህበር የሽማግሌዎች ሰብሳቢ አቶ አዳነ አዳምሰገድ በበኩላቸው በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በባህላዊ እርቅ መፍታት ይገባል።

በጎንደር ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ክስተት በውይይት በመፍታት ተጎጂዎችን መልሶ የማደረጃት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

"ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ የተፈጠረው ክስተት በእጅጉ የሚያሳዝንና ከኢትዮጵያውያን እሴት፣ ባህልና እምነት ያፈነገጠ አሳፋሪ ተግባር ነው" ብለዋል።

ድርጊቱ ሀገር እንዳትረጋጋ ብሎም የከፋ አደጋ ላይ እንድትወድቅ በሚፈልጉ የአሸባሪ አካላት የተፈጸመ ፀያፍ ስራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንፁሃን ዜጎች ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ጭፍጨፋ መፈጸሙ የሚወገዝ ነው ብለዋል።

የተፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት የትኛውንም ህዝብ የማይወክል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ፅንፈኝነት ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባና በአጥፊዎቹ ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አብራርተዋል።

''አሁን ላይ የሰላም መደፍረስ የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር ሆን ተብሎ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር የሰላም ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሃጂ ማሩፍ ኑርሁሴን ናቸው።

''ኢትዮጵያ ስትነካ እንነካለን እንሞታለን'' መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሰላም የማስፈንና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራውን ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

ለሀገራችን ሰላምና ልማት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም