የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የጥፋት ሀይሎችን እናጋልጣለን – የወጣት ሊግ አባላት

113

አምቦ፤ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ለህግ የበላይነት መከበርና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን አሉ የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶች ሊግ አባላት፡፡

ወጣቶቹ በአምቦ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄደዋል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ሊግ አባላት ባካሄዱት ውይይት የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

“ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት በህዝቦች መካከል ግጭት እየፈጠሩ ያሉት አሸባሪው የሸኔ ቡድንና ጽንፈኞችን በአንድነት ተባብረን ሴራቸውን እናከሽፋለን” ብለዋል።

“በኦሮሞ ህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ እኛ ካልመራናት ሀገር ትፈርሳለች እያሉ በሽብር ተግባር የተሰማሩ የጥፋት ሀይሎች በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነት ስለሌላቸው ተባብረን እናጠፋቸዋለን” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ሀገርና ህዝብን ለማዳን በሽብርተኛው ሸኔ ላይ እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡

መንግስትም የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለወጣቱ የስራ እድል እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡

“በትግላችን የተገኘው ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ በመንከባከብና በመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ” ሲሉ በጋራ ቃል ገብተዋል፡፡

“የህዝብ ጠላት የሆነው አሸባሪውን ሸኔና የጽንፈኛ ቡድኖችን የምንሸከምበት ጫንቃ የለንም” ያለው ደግሞ የምእራብ ሸዋ ዞን ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ወጣት ኡርጌሳ ዳመነ ነው፡፡

“ሸኔ በየቦታው የጥፋት ድርጊት በመፈፀምና ህዝቡን ለመለያየት የሚሰራ አጥፊ ቡድን  በመሆኑ ወጣቶች በተባበረ ክንድ መመከት ይጠበቅብናል”ብሏል፡፡

ውይይቱ የዞኑ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ በቂ ግንዛቤ ጨብጠው በጸጥታ ማስከበር ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል አላማ ያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የዞኑ ሀላፊ አቶ ሙሉወርቅ አመና ናቸው፡፡

የዞኑ ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የሀገር ሉዓላዊነት ተከብሮ እንዲቀጥል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ላይ በሀገር ላይ የተቃጣውን ሴራ ለማክሸፍ  በንቃት እንዲሳተፉ አስገንዝበዋል፡፡

 አሸባሪ ቡድኑ ልጅን ከአባት፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ህዝብን ከህዝብ ከመከፋፈል በስተቀር ኦሮሞን እንደማይወክል ወጣቶቹ በውይይታቸው አመልክተዋል።