የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያከናወነውን የማስፋፊያ ግንባታ አጠናቀቀ

90

አዳማ፤ ሰኔ 21/2014(ኢዜአ) የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያከናወነውን የማስፋፊያ ግንባታ ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በ2014 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና በ2015  ዓ.ም እቅድ ላይ ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

የዲጂታል ቤተመፃሕፍትና ወርክሾፖች፣ የከፍተኛ አመራር የስልጠና ማዕከል፣ የተሟላ የመኝታና የምግብ አገልግሎት ህንፃዎች የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሪያድ ዳውድ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር መርሐ ግብር በተጓዳኝ የክልሉን ከፍተኛ አመራር አቅም ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል የስልጠና ማዕከል ግንባታ ማጠናቀቅ ተችል።

ማዕከሉ በየደረጃው ላሉት አመራሮች ተከታታይ የክህሎትና አቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠትና ለማብቃት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

ማዕከላቱ የዲጂታል ላይብረሪ የተሟላለት መሆኑን አመልክተው፤ የዩኒቨርስቲውን የሀብት አስተዳደርና አያያዝ ሶፍት ዌር በማበልጸግ መንግስት የጀመረውን ሪፎርም በሙሉ አቅም ለመደገፍ የሚያስችለውን ቁመና ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞች ባሻገር አዳዲስ የስልጠና ማኑዋሎች እየተዘጋጁ መሆኑን አመልክተው፤ አመራሩንና ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ በተከታታይ በአዳማና ባቱ ካምፓስ ለማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የመልካም አስተዳድርና የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን ለመፍታት ከክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት የጥናትና ምርምር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

"በተለይ በክልሉ የሪፎርምና ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት በየደረጃው ያሉ ሰራተኞችና አመራሩ በአቅም ግንባታ፣ በፖሊሲ ማማከር፣ በጥናትና ምርምር ላይ በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል።

የክልሉን ገቢ ለማሳደግ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ ባቱና ሻሸመኔ የስራ ዕድል አማራጮች ልየታ ጥናትና ማስፈፀሚያ ስልቶችን የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የስቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችንም እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

"ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማክሰም የሚያስችሉ የፖሊስና ስትራቴጂ ጥናቶች ከክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እየሰራን ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም የዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃን ጨምሮ ከዘጠኝ የክልሉ መስሪያ ቤቶች ጋር የሪፎርም፣ የማማከርና የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርስቲው  በቂ የስልጠናና ምርምር መሰረተ ልማቶች የማስፋፊያ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉንም አመልክተዋል።

የ2014 ዓ.ም የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2015  ዓ.ም እቅድ ላይ ሲመክሩ የነበሩት  የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት  በአዳማ ካምፓስ ከ500   ችግኞችን ተክለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በ4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ20 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱንም ፕሬዘዳንቱ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም